መደመር በሁሉም ዘርፎች ተጨባጭ ለውጥ ያመጣ ሀገር በቀል እሳቤ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
መደመር በሁሉም ዘርፎች ተጨባጭ ለውጥ ያመጣ ሀገር በቀል እሳቤ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 3/2018 (ኢዜአ):- የመደመር እሳቤ በሁሉም ዘርፎች ለተመዘገቡ ተጨባጭ ስኬቶች መሰረት የሆነ አገር በቀል እሳቤ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (OBN) ጋር ባደረጉት ቆይታ የመደመር እሳቤ ከባዕድ የተቀዳ ሳይሆን የሀገር በቀል አስተሳሰብና የፍልስፍና ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።
በህዝብ ትግል ስም የኦሮሞን ህዝብ ወደ ብሶት ለመክተት ከንቱ ጥረት የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውን በማንሳት፤ መደመር በሕዝብ ትግል ስም የሚደረግ የለቅሶ ፖለቲካ ያስቀረ እሳቤ መሆኑንም ጠቁመዋል።
እውነተኛ የፖለቲካ መሪ ዋና ተግባር ህዝብን ከገባበት ችግርና መከራ አውጥቶ ወደ በጎና የተሻለ ህይወት ማሸጋገር መሆኑን ነው ያስረዱት።
በኢኮኖሚው ዘርፍ የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎችን በተመለከተ ባብራሩበት ወቅት፣ በኦሮሚያ ክልል በመስኖ ልማት ትልልቅ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል።
ለዚህም በቦረናና በባሌ ዞኖች የተመዘገበው ውጤት ጥሩ ማሳያ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በቅድመ-መደበኛ ትምህርት ቤቶችን በማስፋፋት ረገድም ትልቅ ስራ መከናወኑን አብራርተዋል።
በሌላ በኩል በመደመር እሳቤ በውጭ ጉዳይ ዘርፍ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነትና ገጽታ ያሳደጉ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በመደመር እሳቤ ዋናው መርህ ወደ ኋላ መመልከት ትምህርት ለመውሰድ ብቻ መሆኑንም ተናግረዋል።
የመደመር ሀሳብ የያዘው መጽሐፍ በ10 የተለያዩ ቋንቋዎች መተርጎሙንና ሀሳቡ በተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ማየት መቻሉን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ የመደመር እሳቤ በሁሉም ዘርፍ የሪፎርም ስራዎች ውስጥ ውጤት እንዲመጣ ወሳኝ ሚና መጫወቱን አመልክተዋል።