ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ህዝብ በምርጫው ስልጣን የሚገኘው በዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ መሆኑን አረጋግጧል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ3/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ህዝብ በምርጫው ስልጣን የሚገኘው በዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ መሆኑን ለወዳጅም ለጠላትም አረጋግጧል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (OBN) ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በምርጫው ንቁ ተሳትፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

በምርጫው የተመዘገበው ከፍተኛ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት በአፍሪካ ደረጃም ቢሆን ትልቅና ታሪካዊ ክስተት ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ዓይነቱ የህዝብ አመኔታና ድምፅ ደግሞ ከፍተኛ አገራዊ ኃላፊነት የሰጠ መሆኑን አብራርተዋል።

ህዝቡ በምርጫው የሰጠው ድምፅ እስካሁን ለተከናወኑት ስራዎች እውቅና የሰጠበት መሆኑን ገልጸው፤ ይህ እውቅና ለቀጣይ ሀገራዊ ሃላፊነቶች ትልቅ የቤት ስራ የሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።

በምርጫው የኢትዮጵያ ህዝብ ለጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያለውን ከፍተኛ ቁርጠኝነት በግልጽ ማሳየቱንም ነው ያነሱት።

በምርጫው ታሪክ እንሰራለን ብለን ተናግረን ነበር፣ ህዝባችንም አላሳፈረንም ፤ ታሪክ ሰርቷል ብለዋል።

በዚህም ስልጣን የሚገኘው በዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ መሆኑን ለወዳጅም ለጠላትም አረጋግጧል ብለዋል።

በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉበት ትልቅና አሳታፊ ምርጫ ማካሄድ መቻሉ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሂደት መጠናከር ትልቅ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም