ሰላምን ለማፅናት በቅንጅት የተሠራው ሥራ ክልሉን ወደ ተሟላ ሰላም እየመለሰው - ኢዜአ አማርኛ
ሰላምን ለማፅናት በቅንጅት የተሠራው ሥራ ክልሉን ወደ ተሟላ ሰላም እየመለሰው
ባህር ዳር፤ ነሐሴ 2/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ሰላምን ለማፅናት በቅንጅት የተሠራው ሥራ ክልሉን ወደ ተሟላ ሰላም እየመለሰው መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ገለጸ።
የክልሉ ፖሊስ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ የውይይት መድረክ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው።
በወቅቱም የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት በክልሉ ሰላምን ለማጽናት በተሻለ ቅንጅት የተሠራው ሥራ ክልሉን ወደ ተሟላ ሰላም እየመለሰው ይገኛል።
በሰላም ማስከበር ሥራው ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር የክልሉን ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት የማረጋገጥ ሥራ ሠርቷል ብለዋል።
ለተገኘው አስተማማኝ ሰላምም ኅብረተሰቡ ከፖሊስ ኃይሉ ጎን በመሆን የጽንፈኛ ኃይሉን ሴራ በማጋለጥና የመረጃ ምንጭ በመሆን ከፍተኛ ድርሻ ማበርከቱን ገልጸዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሪፎርም ሥራ ከመሥራት ባሻገር፣ የክልሉን ሰላምና ደኅንነት በማረጋገጥ ብሎም የተገኘውን ሰላም በማጽናት ረገድ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል።
እንዲሁም ተቋሙን ወደ ዲጂታላይዜሽን በመቀየር፣ በምርመራ፣ ወንጀል በመከላከል፣ በአስተዳደር ልማት ሥራና ሠራተኛን በማገናኘት በኩል ጉልህ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።
ሕዝቡ ከፖሊስ የሚፈልገውን አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ ረገድም የተጠናከረ፣ ያደገና የተለወጠ የፖሊስ ተግባራትን ማከናወን መቻሉን አስረድተዋል።
ባለፈው ዓመት የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በማጠናከር በ2019 በጀት ዓመት የፖሊስ ኃይሉ በየትኛውም የግዳጅ ቀጠና የክልሉን ሕዝብ ሰላም የማረጋገጥ ሥራውን የበለጠ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ኮሚሽነሩ አረጋግጠዋል።
አሁን የተገኘውን ሰላም ዘላቂነት በማረጋገጥ በኩል ሕዝቡ ከምንጊዜውም በላይ ለፖሊስ እያደረገ ያለውን ትብብርና ድጋፍ የበለጠ እንዲያጠናክርም አሳስበዋል።
በመድረኩም በዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና በዕቅድ ትውውቅ በየደረጃው የሚገኙ የፖሊስ አመራሮች እየተሳተፉ ሲሆን መድረኩ ነገም የሚቀጥል ይሆናል።