ቀጥታ፡

ምክክሩ መጪው ትውልድ የሰላምና የአብሮነት ተምሳሌት የሆነች ኢትዮጵያን እንዲረከብ መደላድል የሚፈጥር ነው - ተመካካሪ ወጣቶች                    

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2018 (ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ መጪው ትውልድ የሰላምና የአብሮነት ተምሳሌት የሆነች ኢትዮጵያን እንዲረከብ መደላድል የሚፈጥር መሆኑን ተመካካሪ ወጣቶች ገለጹ፡፡    

ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ ተወካዮች የተሳተፉበትና በስምንት ዋና ዋና ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የሚያተኩረው፣ ሐምሌ 08 ቀን 2018 ዓ.ም. የተጀመረው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተመካካሪ ወጣቶች፤ ምክክሩ አሳታፊና አካታች ከመሆኑም ባሻገር መጪው ትውልድ አንድነቷን የጠበቀችና ሰላሟ የጸና ሀገር እንዲረከብ መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።

ከተመካካሪዎቹ መካከል ወጣት ሊዲያ ዮሴፍ፤ ምክክሩ ሁሉም ተሳታፊዎች ሀሳባቸውን ያለገደብ የሚያንጸባርቁበት አውድ መፍጠሩን ተናግራለች።

ሀገራዊ ምክክሩ ለቆዩ ችግሮችና አለመግባባቶች መንስኤ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በዘላቂነት መፍትሔ ለማግኘት የሚያስችል መደላደል እንደሚፈጥር ያላትን እምነት ገልጻለች።

ሌላኛው ተመካካሪ ወጣት እሸቱ ኢረቦ በበኩሉ፤ ምክክሩ ወጣቶች ሰላሟ እና አንድነቷ የጸና ሀገር እንዲረከቡ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ተናግሯል።

ምክክሩ በሀገር ግንባታ ሂደት ወጣቶች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ዕድል መፍጠሩን እና ይህም ለሀገር ሰላምና እድገት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አስረድቷል።

ተመካካሪ ወጣት ገነት አዳኝ፣ የምክክሩ መድረክ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የሰለጠነ የምክክር ባህል መሰረት የሚጣልበት መሆኑን ገልጿል።

ሂደቱ መጪው ትውልድ የሰላምና የአብሮነት ተምሳሌት የሆነች ኢትዮጵያን እንዲረከብ የሚያስችል አገራዊ ፋይዳ እንዳለውም ነው የተናገረችው።

ተመካካሪ ወጣት ያሲን ሃንፈር የምክክሩ መድረክ ኢትዮጵያውያን ለችግሮቻቸው በአንድ ጣራ ሥር ተሰባስበው በጋራ የሚመክሩበት አውድ መፍጠሩን ገልጿል።

ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ ያልነበረ እና አሁን የተገኘ ትልቅ ድል መሆኑን አንስቷል።

የበለጸገች ሀገር የመገንባት ሀገራዊ ራዕይ ከግብ እንዲደርስም ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብሏል።

በምክክሩ ሁሉም እኩል ተሳታፊ እንዲሆን መደረጉ ደግሞ ለሀገር ግንባታ ወሳኝ እርምጃ መሆኑንም አብራርቷል።

  

 

 

   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም