ቀጥታ፡

መነጋገራችን፣ መመካከራችንና መደማመጣችን ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የመግባባት ምዕራፍ ያሻግራል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2018 (ኢዜአ)፦ መነጋገራችን፣ መመካከራችንና መደማመጣችን ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የመግባባት ምዕራፍ ያሻግራታል ሲሉ የዳያስፖራ ማህበረሰብና የሲቪል ማህበረሰብ የሕዝብ ወኪል ተመካካሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል። 

ተመካካሪዎች ጉባኤው አካታች፣ ሀሳብን በነፃነት የሚገልጹበትና ለዘላቂ ሰላም መሠረት የሚጥል መሆኑን ገልጸዋል።

የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የዳያስፓራ ማህበረሰብ ወኪል ተመካካሪ አቶ ልዑልሰገድ አበበ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በምክክሩ የሀሳብ ልዩነቶች በንግግርና በመደማመጥ ወደ የጋራ መግባባት እየተቃረቡ ነው። 

ከጉባኤው የሚፈልቀው የጋራ ሀሳብም በአንዳንድ አካባቢዎች ለግጭት መንስኤ የሆኑ ልዩነቶችን በመፍታት ለቀጣዩ ትውልድ ሰላምን ማስረከብ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ሌላው ተመካካሪ የዳያስፖራ ማህበረሰብ ወኪል ተማካካሪ ጌትነት ለማ፤ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ከትንንሽ የውይይት ቡድኖች ጀምሮ በከፍተኛ መደማመጥና በአካታች አሠራር እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል። 

በኢትዮጵያ ታሪክ እንደዚህ ዓይነት ዕድል አግኝተው እንደማያውቁ ጠቁመው፤ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ህብረት እንደሚያመጣ ተናግረዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ወኪል ተመካካሪ ደሳለኝ ክፍሉ በበኩላቸው፤ የምክክር ጉባኤው ሀሳብ በነፃነት የሚንሸራሸርበትና ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የጋራ መግባባት የሚያሻግር መሆኑን ገልጸዋል። 

ምክክሩ ለቀጣዩ ትውልድ ሰላማዊ፣ የተረጋጋችና የተባበረች ሀገር ማስረከብ የሚያስችሉ የጋራ ሀሳቦች የሚፈልቁበት መድረክ መሆኑንም ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም