ቀጥታ፡

ሴቶች በተፈጥሮ የተሰጣቸውን ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታትና የማስታረቅ ልምድ በፖሊሲና በአሰራር መደገፍ ይገባል 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2018 (ኢዜአ)፦  ሴቶች በተፈጥሮ የተሰጣቸውን ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታትና የማስታረቅ ልምድ በፖሊሲና በአሰራር መደገፍ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዮሃንስ አድገህ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የሴቶች በሰላምና ደህንነት ያላቸውን ገንቢ ሚና ማጎልበትም ለሀገራዊ ልማትና ዕድገት ወሳኝ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ከአፍሪካ ሴቶች ሰላምና ደህንነት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የሴቶችን በሰላምና ደህንነት ያላቸውን ሚና ለማጠናከር ያለመ ሁለተኛውን ዓመታዊ የምርምር አውደ ጥናት አካሂዷል።

የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዮሐንስ አድገህ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ተቋሙ ባለፉት አምስት ዓመታት በሴቶች ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ዙሪያ ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት ሲሠራ ቆይቷል። 

ሴቶች ለሀገር፣ ለክልልና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዕድገትና ሰላም ያላቸው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ገልጸው፣ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታትና በማስታረቅ ረገድ ሴቶች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።

በግጭት ወቅት ሴቶች በተለይ ለጉዳትና ለችግር ተጋላጭ ቢሆኑም፣ ለዓለም ሰላምና ብልጽግና ያላቸውን ወሳኝ ሚና ማጎልበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የአፍሪካ ሴቶች ሰላምና ደህንነት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ታደለች ሃይለሚካኤል በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የሴቶችን ንቁ ተሳትፎ ማጎልበት ለሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ሴቶች ያላቸውን የማስታረቅ ባህልና የሰላም ፍላጎት በፖሊሲና በአሠራር መደገፍ፣ በሽምግልናና በግጭት አፈታት ሂደቶችም በንቃት ማሳተፍ የበለጸገችና ሰላማዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ያግዛል ብለዋል።

የሴቶችን ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ ማጎልበት ሰላምን ለማስፈን ለሚደረገው ጥረት መሠረት በመሆኑ፣ ሴቶችን የሰላም ግንባታ አጋር ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ሴቶች በፖሊሲ አውጪና አስፈጻሚ አካላት፣ እንዲሁም በትምህርትና ምርምር ተቋማት ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባም ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሴቶች ሰላምና ደህንነት ኢንስቲትዩት ከትምህርት ተቋማትና ከፖሊሲ አውጪዎች ጋር በመተባበር ሴቶችን በጥናትና ምርምር ዘርፍ ንቁ ተሳታፊ ለማድረግ እንደሚሠራ አስታውቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም