ቀጥታ፡

የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ሁሉን አቀፍና አካታች በመሆኑ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን የሚያጸና ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2018 (ኢዜአ)፦ የሀገራዊ ምክክር ጉባዔው በሁሉን አቀፍነቱና አካታችነቱ ረገድ ታይቶ የማይታወቅ ከመሆኑም በላይ፣ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን የሚያጸና መሆኑን ተመካካሪዎች ገለጹ። 

የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተመካካሪዎች እንደተናገሩት፤ ምክክሩ ሁሉን አቀፍ እና አካታች፣ መደማመጥና መከባበር የሚስተዋልበት እና ዲሞክራሲያዊ አካሄድ የታየበት እደሆነ ይገልጻሉ። 

ከተመካካሪዎቹ መካከል አቶ መሃሙድ መሃመድ እንደገለጹት፤ መድረኩ ሁሉን አቀፍ እና አካታች በመሆን ረገድ ታይቶ የማይታወቅ ነው ብለዋል።

በምክክሩም የሚነሱ ሃሳቦች ያለ ልዩነት በእኩል መንገድ የሚስተናገዱበት ሁኔታ በመኖሩ ተመካካሪው በነጻነት ሃሳቡን እንደሚገልጽ ተናግረዋል።

ከምክክሩ በኋላ ኢትዮጵያ ሰላም፣ እኩልነት እና ፍትህ የሰፈነባት እንደምትሆን ያላቸውን ብሩህ ተስፋ ገልጸዋል። 

ሌላኛዋ ተመካካሪ ወይዘሮ አስቴር ዳንኤል እንደተናገሩት፤ ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ሰላምን፣ አንድነትን እንዲሁም ፍቅርን እንደሚያመጣ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። 

የምክክሩ ሂደት እንደ ሃገር ያሉብንን አለመግባባቶች ለመፍታት፣ በጋራ የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ መወያየት፣  መደማመጥና መከባበር የሚስተዋልበትን ድባብ እንደፈጠረ አንስተዋል።

ለቀጣዩ ትውልድ ሰላም የሰፈነባት ሃገርን ለማስረከብ ምክክሩ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል። 

ሌላኛው ተመካካሪ አቶ ሙሉዓለም ጌታሁን እንደገለጹት፤ ምክክሩ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተቀረጹ አጀዳዎች ላይ ለውይይት አመቺ በሆነ መልኩ፣ ሰፊ የሆኑ ሃሳቦች በነጻነት እና በዲሞክራሲያዊ መንገድ እየተስተናገዱ እንደሆነ ገልጸዋል።

ምክክሩም አሳታፊ በሆነ መንገድ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ያካተተ እና ለምናደርገው የሀገረ መንግስት ግንባታ ትልቅ መሰረት የምንጥልበት ነው ብለዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም