በምክክር እንጂ በመሳሪያ ድምጽ ሀገር አይገነባም - ኢዜአ አማርኛ
በምክክር እንጂ በመሳሪያ ድምጽ ሀገር አይገነባም
ኢትዮጵያ የዛሬ ማንነቷና ሉዓላዊ ክብሯ ተጠብቆ እዚህ እንድትደርስ በርካታ ውጣውረዶችን አልፋለች። በቀደመ ታሪኳም ዜጎች በራሳቸው የውስጥ ጉዳይ መስማማት ባለመቻል እርስ በእርስ ካደረጓቸው ግጭቶች ባለፈ የውጭ ሃይሎችም የራሳቸውን አሉታዊ ጫና ሲፈጥሩ ቆይተዋል፤ አሁንም ይህንኑ ለማስቀጠል ተላላኪዎቻቸውን ለመጠቀም ሲሞክሩ ይታያል።
በአንድ ሃገር ውስጥ የማያግባቡ ጉዳዮች በየትኛውም አጋጣሚና የታሪክ ምዕራፍ ሊያጋጥሙ ይችላሉ። እነዚህን ችግሮች በሃይል ለመፍታት የሚደረገው የመሳሪያ ትንቅንቅ ግን አክሳሪና ዘመን እያለፈበትም ነው። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን ሰላማዊ የእድገት ጉዞ ለማወክ የህዝቦቿን አንድነት ለመበጥበጥ ከቅርብም ሆነ ከሩቅ የሚመጡ ጠላቶች ጠፍተው አያውቁም።
በየዘመናቱ የተሻገርናቸው የታሪክ ስብራቶችን ፣ የመብት ጥያቄዎችንና ሌሎችንም መነሻ በማድረግ በውስጥ ባንዳዎች እና በውጭ ባዳዎች አማካኝነት የማያቋርጥ ጦርነት ውስጥ ለመክተት፣ የብልጽግና ጉዞዋን ለማደናቀፍ የሚደረጉ ሴራዎች ዛሬም ላይ ቀጥለዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላት ተሰሚነትና ተጽዕኖ የሚያሳምማቸው ለዜጎቿን እኩል ተጠቃሚነትና ብልጽግና መረጋገጥ የምታደርገው ጥረት የሚያስጨንቃቸው እነዚህ ሃይሎች በመብት ፣ በነጻነት፣ በዴሞክራሲ፣ በማንነትና በሌሎችም የሃሰት ትርክቶች መነሻነት በሩቅ ቢያቅታቸው በቅርብ የውስጥ ተላላኪ ባንዳዎችን እያደራጁ በጀት መድበው የጦር መሳሪያ አቅርበው ሀገር የማፍረስ ሙከራቸውን አላቋረጡም።
በመደመር እሳቤ ሁሉንም በአንድ ላይ በማቀራረብና የጋራ ትርክቶችን በመገንባት ከልዩነት ይልቅ የሚያቀራርቡ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ዘላቂ ልማቷን መፃኢ ብሩህ ተስፋዋን ለማለምለም በሁሉም ዘርፍ ኢትዮጵያ በዜጎቿ ተሳትፎ እየሰራች መሆኗም ምቾት ነስቷቸዋል።
በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሔደ ያለውና ወርቃማው እድል ሃገራዊ ምክክር ልዩነቶችን በምክክር ለመፍታት ፣ የሚያስችሉ ወሳኝ ምዕራፎች ላይ ደርሷል ። በዚህ የምክክር ሒደት በሀገሪቱ የትኛውም ጥግ ያለ ዜጋ እንዲሁም በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተወከሉበት ፣ የብሔር፣ የፖለቲካ አመለካከትና የሃይማኖት ልዩነት የማያደናቅፉት ሁሉንም ያሳተፈ ምክክር እየተካሔደ ይገኛል።
ጥያቄያችንን በጠብመንጃ አፈሙዝ እንፈታለን ያሉ ታጣቂዎችም ብረት በማስቀመጥ አጀንዳዎቻቸውን ይዘው ወደ ጠረጴዛው ቀርበዋል። ልክ ናቸው ሀገር ከሁሉም ነገር ትበልጣለችና ይሄንን ወርቃማ እድል ለመጠቀም ማሰብ ትክክለኛው ውሳኔ ነው።
በትጥቅ ትግል ጥያቄያችንን እንመልሳለን በሚል ሽፋን የሌሎችን አጀንዳ ለማሳካት የሚደረግ ጥረት የሃገርና የትውልድ ጠባሳ ከማስቀመጥና የታሪክ ተወቃሽ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ እንደማይኖረው መገንዘብ ብልህነት ነው።
የዚህ ምክክር ተሳታፊ/ተመካካሪ ከሆኑት የቀድሞ ታጣቂዎች መካከል የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት(አፋሕድ) አመራር ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ በዚህ ይስማማሉ ። ሀገራዊ ምክክር ትልቅ ተስፋ የጣልንበት፣ በንግግር፣ በምክክር ሀገራችንን የምናስቀጥልበት፣ ሁሉም ተነጋግሮ ተመካክሮ የወደፊቷን ኢትዮጵያ ከችግሮች ነፃ የሚያደርግበት ነው ይላሉ።
ምክክሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚነጋገርበት፣ የሚመካከርበት እና በሃሳብ የበላይነት ጠንካራ ሃገር የሚፈጠርበት መልካም የታሪክ አጋጣሚ መሆኑንም ይናገራሉ።
በምክክር፣ በድርድር የሕዝብን ጥያቄ በመመለስ ሀገርን የምናስቀጥልበትና የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት የምናስወግድበት በመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ተስፋ የጣለበት ነው ብለዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አመራር የቀድሞ ታጣቂ ጃል ሰኚም ይሄንኑ ሃሳብ ይጋራሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ ለዓመታት የቆዩ ልዩነቶችን ለመፍታት ሀገራዊ ምክክር መዘጋጀቱ ትልቅ እርምጃ እንደመሆኑ እሳቸውም ያላቸውን ሀሳብ በማንጸባረቅ እየመከሩ ይገኛሉ።
እርሳቸውና ቡድናቸው ከዚህ ቀደም የትጥቅ ትግልን በመምረጥ ጫካ ገብተው እንደነበር አስታውሰው፤ ችግሮችን በመሳሪያ ከመፍታት ይልቅ በሰላማዊ የምክክር መድረክ መፍታት ጥሩ አማራጭ መሆኑን አምነው ወደ ሰላም መንገድ መምጣታቸውንም ተናግረዋል።
ችግሮቻቸውን በምክክር የፈቱ ሀገራት በሁሉም ዘርፍ ዕድገታቸውን የሚያስቀጥሉ ሲሆኑ ወደ ትጥቅ ትግል ያመሩና ግጭት ውስጥ የገቡት ደግሞ በፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውድቀት ለከፋ ድህነት መዳረጋቸውን ጠቅሰዋል።
የጦር መሣሪያ በመነቅነቅና ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ በመግባት የሚፈታ ችግር እንደሌለ የሚናገሩት ደግሞ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ(አብን) አመራሩ ተመካካሪ ጣሒር መሀመድ ናቸው።
ጫካ ባለውና እዚህ ባለው ሰው መካከል ምንም ዐይነት የዜግነት ልዩነት እንደሌለ ገልጸው ከትጥቅ ትግል ይልቅ በሃሳብ ለመታገል ልዩነቱን ለማቅረብ የፈለገ ሁሉም ዜጋ በምክክሩ የመሳተፍ ነጻነት እንዳለው ገልጸዋል።
በሃገራዊ ምክክሩ ከትጥቅ ትግል ይልቅ በሰላማዊ መድረክ መወያየት የተመረጠበት ዋና ምክንያት ዘላቂ ሰላም፣ አገራዊ መግባባት እና የፖለቲካ ባህል ለውጥ ለማምጣት ነው::
የትጥቅ ትግል የዜጎችን ህይወት ያጠፋል፣ መሰረተ ልማቶችን ያወድማል፤ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውድቀትንም ያመጣል: ፤ ሰላማዊ መድረክ ግን ያለምንም ደም መፋሰስ ሃሳብን በሃሳብ ለመሞገት እድል ይሰጣል::
በኃይል የሚመጣ ለውጥ ብዙውን ጊዜ አሸናፊና ተሸናፊን ስለሚፈጥር የቁስል እና የቂም ዑደትን ያስቀጥላል:: በሰላማዊ ውይይት የሚገኝ መፍትሄ ግን የሁሉንም ወገን ስጋት እና ፍላጎት ያገናዘበ በመሆኑ ዘላቂነት ይኖረዋል:: ሃገራዊ ምክክሩ የታጠቁ አካላትም ጭምር መሳሪያቸውን አስቀምጠው በሃሳብ እንዲፎካከሩ መንገድ ከፍቷል።
ይህ ታሪካዊና ወርቃማ እድል ኢትዮጵያዊንን አግባብቶ ወደተረጋጋችና የበለጸገች ሃገር የሚመራ በመሆኑ ስኬታማነቱ አያጠራጥርም። ለእድለኛው ትውልድ ያጋጠመው ወርቃማው ስጦታ ሃገራዊ ምክክር የተቋቋመለትን ዓላማ ያሳካል።