ብሩኖ ጉማሬሽ አርሰናልን በይፋ ተቀላቀለ - ኢዜአ አማርኛ
ብሩኖ ጉማሬሽ አርሰናልን በይፋ ተቀላቀለ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2018 (ኢዜአ)፦ የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል የኒውካስል ዩናይትድ አምበል የነበረውን የ28 ዓመቱን የብራዚል ብሔራዊ ቡድን አማካይ ብሩኖ ጉማሬሽን ዝውውር ማጠናቀቁን ዛሬ ይፋ አድርጓል።
የወቅቱ የፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን የሆነው አርሰናል ለተጫዋቹ ዝውውር የ75 ሚሊዮን ፓውንድ ክፍያ የፈጸመ ሲሆን፣ ጉማሬሽም ተጨማሪ የአንድ ዓመት ማራዘሚያ አማራጭ ያለው የአራት ዓመት ውል ተፈራርሟል።
በሚኬል አርቴታ ስብስብ ውስጥ 39 ቁጥር ማሊያን ለብሶ ይጫወታል።
ብሩኖ ጉማሬሽ ዝውውሩን አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት አርሰናልን መቀላቀል የፈለገው አዲስ ፈተናን ለመጋፈጥ እና ትላልቅ ዋንጫዎችን ለማንሳት መሆኑን ገልጿል።
የ28 ዓመቱ ተጫዋች እ.አ.አ ጁላይ 2026 ላይ አርሰናልን ለመቀላቀል በግሉ ተስማምቶ እንደነበር የሚታወስ ነው።
አሁን ላይ ጉማሬሽ አርሰናልን መቀላቀሉ የተንዛዛውን የዝውውር ጉዳይ እንዲቋጭ አድርጎታል።
ጉማሬሽ እ.አ.አ በ2022 ከሊዮን ወደ ኒውካስትል ዩናይትድ በመዘዋወር ሲጫወት ቆይቷል።
ተጫዋቹ መድፈኞቹን መቀላቀሉ የቡድኑን የአማካይ ክፍል ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ይጠበቃል።
ብሩኖ ጉማሬሽ ከክሪስቶስ ዞሊስ እና ኢላን ሜስሊዬር በመቀጠል አርሰናል በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት የተቀላቀለ ሶስተኛ ተጫዋች ሆኗል።