የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሮች ምቹ አካባቢን በመፍጠር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ አስችለዋል - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሮች ምቹ አካባቢን በመፍጠር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ አስችለዋል
ጂግጂጋ፤ ነሐሴ 2/2018 (ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሮች ምቹ አካባቢን በመፍጠር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ አስችለዋል።
3ኛው ዙር የአካባቢ ብክለት መከላከል ክልል አቀፍ ንቅናቄ ''ፅዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ'' በሚል መሪ ሐሳብ በጂግጂጋ ተካሄዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ኡስማን እንደገለጹት፣ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሮች ምቹ አካባቢን በመፍጠር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ አስችለዋል።
ጽዱ ኢትዮጵያን እውን ለማድረግም የፕላስቲክ ነክ ተረፈ ምርቶችን፣ የደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ ብክለትን በመከላከል በውሃ እና አፈር ላይ እየተፈጠረ ያለውን ተጽዕኖ ለመቀነስ የወጡ ህጎችና መመሪያዎችን ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም የቆሻሻ ማስወገጃ ዘላቂ ሥርዓቶችን በመገንባት ከተሞች ምቹና ጽዱ እንዲሆኑ በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
የአከባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍሬነሽ መኩሪያ በበኩላቸው፣ መርሃ ግብሩ ባለፉት ሁለት ዙሮች የተገኙ ውጤቶችን በማጠናከርና፣ በማስፋት፣ ጤናማና ንጹህ አካባቢን የመፍጠር ተግባሩን ለማጠናከር ያለመ መሆኑን አመልከተዋል።
''እንዲሁም አካባቢያችንን ለመጠበቅ እና ለመጪው ትውልድ ፅዱ ኢትዮጵያን ለማውረስ ያለንን የጋራ ቁርጠኝነት በድጋሚ ለማረጋገጥም ጭምር ነው'' ብለዋል።
3ኛው ዙር የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ በቀጣዮቹ ሶስት ወራት የሚተገበርና በዋናነት የፕላስቲክ ብክለትን በመከላከል፣ አደገኛ ኬሚካሎችንና ቆሻሻዎች አያያዝን፣ እንዲሁም የድምፅ ብክለትን የመከላከል ተግባራት እንደሚከናወንም አክለዋል።
እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ ፅዱ ኢትዮጵያ በመንግስት ብቻ የሚከወን ባለመሆኑ በየቤታችን፣ በየትምህርት ቤቱ፣ በየመሥሪያ ቤቱና በፋብሪካዎች የምንፈጽማቸው በጎ ተግባራት ተደምረው ትልቅ ሀገራዊ ለውጥ ያመጣሉ።
በዚህም ሁሉም የመንግስት ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ፣ የሲቪል ማህበረሰብ፣ የሚዲያ ተቋማት፣ የሴቶችና የወጣቶች ማህበራት እንዲሁም እያንዳንዱ ዜጋ የዚህ ሀገራዊ ንቅናቄ ባለቤት በመሆን በንቃት እንዲሳተፍም ጥሪ አቅርበዋል።
የሶማሌ ክልል የአካባቢ ጥበቃና ገጠር መሬት አስተዳድር ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ሙህየዲን አብዲ በበኩላቸው በክልሉ ባለፉት ዓመታት በጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄዎች በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ጽዱ አካባቢ ለመፍጠር እየተከናወኑ የሚገኙ በርካታ ተግባራትም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የቢሮ ኃላፊው አረጋግጠዋል።
በመርሃ ግብሩም በክልሉ ፕላስቲክን በመከላከል፣ መመሪያዎችን በመተግበርና ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ውጤታማ የሆኑ ከተሞች የእውቅና መስጠት ሥነ-ሥርዓት ተካሄዷል።