በአማራ ክልል ሕብረተሰቡን በማሳተፍ የተገኘው ሰላም የልማት ተግባራትን ለማፋጠን አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ሕብረተሰቡን በማሳተፍ የተገኘው ሰላም የልማት ተግባራትን ለማፋጠን አስችሏል
ኮምቦልቻ፤ ነሐሴ 2/2018 (ኢዜአ)፦ ሕብረተሰቡን በማሳተፍ የተገኘው ሰላም የልማት ተግባራትን ለማፋጠን አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ገለጸ።
በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች የጋራ የሰላምና የልማት ምክክር መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ ተካሂዷል።
በቢሮው የግጭት መከላከልና አፈታት ዳይሬክተር አቶ መንግሥቱ ፈረደ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ ሕብረተሰብ በማሳተፍ የክልሉን ሰላም ማስጠበቅ ተችሏል።
በዚህም በሰፈነው ሰላም የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ሥራዎችን በማቀላጠፍ ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
ለተገኘው ሰላም መረጋገጥ የአመራሩ ቁርጠኝነት፣ የሕብረተሰቡ የሰላም ፍላጎትና ትብብር እንዲሁም የተዘረጋው ቅንጅታዊ አሠራር ውጤት ማምጣቱን ተናግረዋል።
የምክክር መድረኩ ዋና ዓላማ የሁለቱ ዞኖች አመራሮች በጋራ በመምከርና የቀጣይ አቅጣጫ በማስቀመጥ ሰላምን በዘላቂነት ማስፈን እንደሆነ አስረድተዋል።
ችግሮችን በውይይት፣ በንግግርና በሽምግልና በመፍታት የሕዝቦችን አብሮነት ከማጠናከር ባለፈ የጋራ ሰላም፣ ልማትና መልካም አስተዳደር ማስፈን እንደሚገባም አሳስበዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ይደሰቱ ክፈተው ፤ አመራሩና ሕብረተሰቡ በቅንጅት በመስራታቸው የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ የልማት ተጠቃሚ ማድረግ አስችሏል ብለዋል።
በቅንጅት በተካሄደው የሕግ የማስከበር ሥራ በአካባቢው ሰላምን ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል።
የተገኘውን ሰላም በማጽናት የጋራ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደ ዞን የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።
"ሕብረተሰቡን በማስተባበር የአካባቢያችንን ሰላም መጠበቅ መቻላችን ለልማት ተጠቃሚነት አብቅቶናል" ያሉት ደግሞ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ አወል እንድሪስ ናቸው።
ቀደም ሲል ሕብረተሰቡን በመከፋፈልና ግጭት በመፍጠር የግል ጥቅም ለማጋበስ የሚሰሩ አካላት እንደነበሩ ጠቁመው፣ አሁን ላይ ግን የቀጠናውን ሰላም በጋራ በመጠበቅ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል።
በቀጣይም የተገኘውን ሰላም በማጽናት የሕብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከአጎራባች ዞኖች ጋር በቅንጅት እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
በመድረኩ የሰሜን ሸዋ፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርና የደቡብ ወሎ ዞኖች የፀጥታ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።