ቀጥታ፡

በዞኑ የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን በራስ አቅም ለመቋቋም የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል

ቦረና፤ ነሐሴ 2/2018 (ኢዜአ) ፦ በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ቦረና ዞን የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን በራስ አቅም ለመቋቋም የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን የዞኑ ቡሳ ጎኖፋ ፅህፈት ቤት ገለጸ።

የሚያጋጥሙ ችግሮችን በራስ አቅም ለመቋቋም በተሰራ የሀብት ማሰባሰብ ስራ በሐምሌ ወር ብቻ ከ48 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡም ተገልጿል።

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሊበን ደበሶ እንደገለፁት፤ ችግሮችን በራስ አቅም ለመቋቋም የህዝብ መድረክ በማዘጋጀት በተደረገ ውይይት የጋራ መግባባት መፈጠሩን ገልጸዋል።

በዞኑ 9 ወረዳዎች ከ481 ሺህ 700 በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች የቡሳ ጎኖፋ አባል መሆናቸውን ገልጸው ከአባላትና ከደጋፊዎች ከ179 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የዓይነትና የጥሬ ገንዘብ ሀብት ለማሰባሰብ በማቀድ ወደ ሥራ መገባቱን ጠቁመዋል።


 

ለዚህም በሐምሌ ወር 2018 ዓ.ም ብቻ ከዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ከ48 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የዓይነትና የጥሬ ገንዘብ መሰብሰቡንና ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በተሠራ ሥራ ከ78 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን አስታውሰዋል።

ከዚህ ውስጥ ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆነው የቡሳ ጎኖፋ አባል ያልሆኑ በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች ያደረጉት ድጋፍ መሆኑን ጠቁመው ካለፈው ልምድ በመውሰድ ዘንድሮ ላቅ ያለ የሀብት ማሰባሰብ ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

በዞኑ 8 ወረዳዎች 172 ሄክታር የወል መሬቶችን በተለያዩ ሰብሎች በማልማት ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለመሸጋገር ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።


 

የነገሌ ቦረና ከተማ ነዋሪና የመንግሥት ሠራተኛው አቶ መኮንን ገሽር በግል ፍላጎትና ተነሳሽነት ለቡሳ ጎኖፋ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው ድጋፉ እርስ በእርስ የመረዳዳትና የአብሮነት እሴቶችን የሚያጎለብት መሆኑን ተናግረዋል።

የዚሁ ከተማ ነዋሪ ወጣት ዲባ ዲዳ በበኩሉ "ማኅበራዊ ችግሮችን በራስ አቅም ለመቋቋም በገንዘብ፣ በእውቀትና በጉልበት ሁላችንም ልንተባበር ይገባል" ብሏል።


 

ወጣቱ በራስ ተነሳሽነት የቡሳ ጎኖፋ አባል በመሆን በቋሚነት በየወሩ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጾ "ጥንት አባቶቻችን ያቆዩልን የመተሳሰብ፣ የመረዳዳትና የአብሮነት እሴት በዚህ ዘመንም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት" ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም