በአፋር ክልል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ሰመራ፤ ነሐሴ 2/2018 (ኢዜአ) ፦ በአፋር ክልል የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ገለጹ።
የአፋር ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 5ኛ የሥራ ዘመን፣ 10ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል።
ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ የክልሉን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት ስኬታማ ናቸው።
በተለይም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን የተቻለ ሲሆን፤ በመስኖ ልማትም 142 ሺህ 675 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎችና አትክልቶች መሸፈን መቻሉን ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት በበጀት ዓመቱ ከ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የግብርና ግብዓቶች መሰራጨታቸውን አመልክተው፤ ከዚህ ውስጥም ከ47 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ መደረጉን ገልጸዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በክልሉ ያልለሙ መሬቶችን ወደ እርሻ ሥራ በማስገባት የአርብቶ አደሩና ከፊል አርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ማስቻሉንም ነው ያብራሩት።
በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በማስወገድ በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከ16 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም አስረድተዋል።
የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያን እስከ ታች ድረስ በማውረድና የንቅናቄ ሥራዎችን በማከናወን ከ405 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል በሪፖርታቸው፤ በክልል ደረጃ 80 ሺህ 621 ዜጎች የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና መውሰዳቸውንም ነው ለምክር ቤቱ የገለጹት።