በሲዳማ ክልል የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማትን በማሻሻል ለሕዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማትን በማሻሻል ለሕዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው
ሀዋሳ፤ ነሐሴ 2/2018 (ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማትን በማሻሻል ለሕዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸው ተገለጸ።
የክልሉ ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸሙን ገምግሟል።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ አቶ አሸናፊ ኤልያስ እንዳሉት፣ የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማትን በማሻሻል ለሕዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው።
ከተማን ከወረዳና ከገጠር ቀበሌዎች የሚያገናኙ መንገዶችንና የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት መሰራቱን ጠቁመዋል።
የክልሉ ከተሞች ለኑሮ፣ ለሥራና ለኢንቨስትመንት ምቹ እንዲሆኑ የኮሪደር ልማት ስራን በመስራት፣ የመኖሪያና የኢንቨስትመንት ቦታ በማቅረብ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በከተሞችና በገጠር መካከል ያለውን የእድገትና የልማት ልዩነት ለማጥበብ በገጠር ኮሪደርና ሞዴል መንደሮችን የማስፋፋት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ አሸናፊ ተናግረዋል።
የሲዳማ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብሩክ ሰለሞን በበኩላቸው፣ የክልሉ ከተሞች ደረጃውን በጠበቀ ፕላን እንዲመሩ ለማድረግ በተከናወነው ሥራ የ73 ከተሞች የፕላን ክለሳና አዲስ ፕላን የማዘጋጀት ሥራ መሰራቱን ጠቁመዋል።
በከተሞች የአገልግሎት አሰጣጡን ከማሻሻል አኳያ በሐዋሳ በክልሉና በከተማ አስተዳደሩ «መሶብ» የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ወደ ስራ በማስገባት ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት መቻላቸውን ገልጸዋል።
ይህን ለማስፋት በስድስት ከተሞች የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማዕከላት ግንባታ ተጠናቆ የቁሳቁስ የማሟላት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ በተያዘው የ2019 በጀት ዓመት ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል።
የወንዶገነት ወረዳ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መልካሙ ኤርሚያስ እንዳሉት፣ በወረዳው በከተማና በገጠር መካከል ያለውን የልማት ልዩነት ለማመጣጠን እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በወረዳው የገጠር ኮሪደር ልማትና ሞዴል የገጠር መንደሮችን በማስፋፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተከናወነ ተግባር 13 ሞዴል ቤቶችን መገንባት እንደተቻለ ገልጸዋል።
ወንዶገነት በወሻ ከተማ አቅራቢያ ያሉ የተፈጥሮ ፍልውኃዎችን በአግባቡ አልምቶ የቱሪስት ፍሰቱንና ገቢን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የሴክተሩ የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ላይ የክልሉ አራት ዞኖች ዋና አስተዳዳሪዎች፣ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ፣ የወረዳ አመራሮችና የሴክተሩ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።