ቀጥታ፡

የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ አሲዳማ መሬትን የማከም ተግባር እያከናወነ ይገኛል

ቴፒ፤ ነሐሴ 02/2018 (ኢዜአ)፦ የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችል አሲዳማ መሬትን የማከም ተግባር እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።

ማዕከሉ በምርምር አዳዲስ ዝርያዎችን ከማውጣትና ከማላመድ ባሻገር የአፈር አሲዳማነት ቁጥጥርና ማከም ተግባራትን በማከናወን ለአርሶ አደሮች ችግር ፈቺ መፍትሔዎችን እያቀረበ መሆኑን ገልጿል።

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ደረጀ ቱሉ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ የአርሶ አደሩን የግብርና ሥራ ውጤታማነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ምርታማነትን የሚቀንሱ ምክንያቶችን በጥናት ተከታትሎ ማስወገድ ይገባል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦችና በጋምቤላ ክልሎች በአሲዳማነት የተጠቃ ሰፊ ማሳ መኖሩን ጠቅሰዋል።

"ይህም ምርታማነትን በመቀነስ በአርሶ አደሩ ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመግታት አሲዳማ መሬትን የማከም ሥራ እየሠራን ነው" ብለዋል።

በዘንድሮው ዓመት በክልሉ ከ100 ሄክታር በላይ ማሳ የማከም ተግባር መከናወኑን ገልጸው ከዚህ ውስጥ በየኪ ወረዳ 22 ሄክታር ማሳ ምርት አያያዝ ውጤታማ ሆኖ መገኘቱን አስረድተዋል።

ማዕከሉ አሲዳማ አፈርን በመመርመር በኖራ፣ በቨርሚ ኮምፖስት እንዲሁም በኖራና በተፈጥሮ ኮምፖስት ቅይጥ የማከም ሥራ የሚሠራ ሲሆን፣ በቀጣይም ይህን ተግባር በማጠናከር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ይሠራል ብለዋል።

የአፈር አሲዳማነት በይበልጥ በበቆሎ ምርት ላይ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ ከአንድ ሄክታር ከ20 ኩንታል ያነሰ ምርት እንዲሰጥ እንደሚያደርግ በማዕከሉ የአፈር ለምነት ተመራማሪ ሙሉሰው ወዳጆ ተናግረዋል።

ዝናብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ጎልቶ የሚታየው አሲዳማ መሬት ከታከመ በኋላ ከ70 ኩንታል በላይ የበቆሎ ምርት ወደ መስጠት ደረጃ ተመልሶ እንደሚያገግም ገልጸዋል።

የየኪ ወረዳ ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ኅብረት ሥራ ጽሕፈት ቤት የአዝርዕትና ሰብል ልማት ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ይርጋለም አሰፋ በዞኑ በቆሎ በተስማሚነት የሚለማ ቢሆንም፣ በአሲዳማ አፈር ስለሚጠቃ ምርታማነቱ አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

በምርምር ማዕከሉ የታከመው ማሳ ያመጣውን ውጤት በቀጣይ በሌሎች ማሳዎች ወደተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ለማስፋት ትኩረት አድርገው እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

ከአካባቢው አርሶ አደሮች መካከል የአዲስዓለም ቀበሌ አርሶ አደር መሐመድ ሰኢድ እና ሰሎሞን ኃይሌ፣ የግብርና ምርምሩ ማሳቸውን በኖራ አክሞ ተስፋቸው እንዳለመለመ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በቆሎ ሲዘሩ ግማሹ ሳይበቅል የሚቀርበትና የበቀለውም እየቀጨጨ የሚበላሽበት ሁኔታ ይገጥማቸው እንደነበር ገልጸው አሁን ላይ ማሳው ታክሞ የዘሩት በቆሎ ምርት አያያዝ ከቤተሰብ ፍጆታ ተርፎ ለገበያ መብቃት የሚችል መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም ሌሎች ማሳዎቻቸውን በማሳከም ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ጠንክረው እንደሚሠሩም አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል።

በየኪ ወረዳ አዲስ ዓለም ቀበሌ 22 ሄክታር አሲዳማ መሬት በኖራ ታክሞ 86 አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም ያለሙት የበቆሎ ማሳ ውጤታማነት ተሞክሮ ለሌሎች እንዲጋሩ እየተደረገ መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም