የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽንና የሪፖርታጅ ግሩፕ የልማት ትብብር የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማዘመን ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል - ኢዜአ አማርኛ
የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽንና የሪፖርታጅ ግሩፕ የልማት ትብብር የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማዘመን ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽንና የሪፖርታጅ ግሩፕ የልማት ትብብር የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማዘመን ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ ገለጹ።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ከዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ሪፖርታጅ ግሩፕ ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ሁለገብ የመኖሪያና የንግድ ሕንፃ ለመገንባት የልማት አጋርነት ፕሮጀክት ይፋ አደረጉ።
የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ በዚህ ወቅት፣ አጋርነቱ የተቋማቱን ስትራቴጂያዊ የልማት አጋርነት በማጠናከር የኢትዮጵያና ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ትብብርን የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም የሀገራቱን ጠንካራ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚያስችል ጭምር እንደሆነም ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ዘመናዊ ከተማን በመገንባት የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል።
የፋውንዴሽኑና የሪፖርታጅ ግሩፕ ትብብርም ዓለም አቀፍ አልሚዎች ኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት መዳረሻ የስበት ማዕከል እያደረጓት እንደሚገኝ ማሳያ ነው ብለዋል።
የሪፖርታጅ ግሩፕ ሊቀመንበር አሪፍ ኢስማኤል በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በሀገራቱ መካከል ያለውን ሁለንተናዊ የልማት ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑን ገልጸዋል።
የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሜጀር ጄኔራል ደረጀ መገርሳ፣ ፕሮጀክቱ ከአዲስ አበባ ፈጣን የከተሜነት ዕድገት ጋር የሚመጣጠን ዘመናዊ ግንባታ እንደሚሆን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ለሠራዊቱ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማሟላት ተጨማሪ የገቢ አቅም የሚገነባ መሆኑን አመልክተዋል።
የሪፖርታጅ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሐናን አሕመድ ኑር እንዳሉት፤ በአፍሪካ ሕብረት ዋና መሥሪያ ቤት ፊት ለፊት በ23 ሺህ ካሬ ሜትር የሚገነባውን ፕሮጀክት በሦስት ዓመታት ጊዜ ለማጠናቀቅ ይሰራል ብለዋል።
ሕንፃው 1 ሺህ 86 ስቱዲዮ፣ ባለአንድና ባለሁለት መኝታ የመኖሪያ አፓርታማ፣ የንግድ ሱቆች፣ ጂምናዚየም፣ መዋኛ ገንዳ፣ የስፖርት ማዘውተሪያና ሌሎች ዘመናዊ አገልግሎቶችን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱም በመኖሪያና በንግድ ልማት ብቻ ሳይወሰን ለኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ዘመናዊነት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና ለኢንቨስትመንት መስፋፋት አዲስ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።