ቀጥታ፡

በክልሉ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል

ሆሳዕና፤ ነሐሴ 2/2018 (ኢዜአ) ፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተከናወነው የፍራፍሬ ልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።

በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአካባቢ ጥበቃን ከማረጋገጥ ባሻገር የፍራፍሬ ልማትን በማስፋፋት የዜጎችን የምግብ ዋስትና እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሳደገ ይገኛል።

መርሃ ግብሩ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት የሀገሪቱን የደን ሽፋን በተጨባጭ እያሳደገ መሆኑ እሙን ነው።


 

የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ የተራቆቱ መሬቶችን በማልማትና ለቀጣዩ ትውልድ ምቹ አካባቢን በመፍጠር ረገድ ውጤታማነቱን እያስመሰከረ ይገኛል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ስሩር እንደገለጹት፤ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በፍራፍሬ ልማት የምግብ ዋስትናውን ያረጋገጠና ተጠቃሚነቱን ያሳደገ ቤተሰብ መፍጠር ተችሏል።


 

የአረንጓዴ አሻራ ትግበራው ለምግብነት የሚውሉ ዛፎችን በመትከል ረገድ ተቋማትን ጨምሮ የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማሳደግ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

መርሃ ግብሩ ክልሉ በፍራፍሬ ልማት ያለውን አቅም በአግባቡ እንዲጠቀም ያደረገ ሲሆን የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማሳደግ ረገድም ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበበት እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በሀድያ ዞን የምስራቅ ባደዋቾ ወረዳ ዌራቡሼራ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ኤልያስ መጋቦ በበኩላቸው፤ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 1 ነጥብ 5 ሄክታር የተራቆተ ማሳቸውን አልምተው ለመጠቀም መቻላቸውን ገልጸዋል።


 

ማሳቸውን በአቮካዶ፣ በሙዝ፣ በሌሎች የፍራፍሬና የቅመማ ቅመም ሰብሎች በማልማትም ውጤታማ መሆን  መቻላቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ምርትና ምርታማነታቸው እያደገ በመምጣቱ ያመረቱትን ከቤተሰብ ፍጆታ አልፎ ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዳሳደጉ ገልጸዋል።

የሆሳዕና ከተማ የሄጦ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ትግስት አጋፋሪ፤ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተሳትፎ በማድረግ በውስን መሬት ላይ ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን ማልማታቸውን ነው የሚናገሩት።


 

ከዚህ ውስጥም የተከሉት የአቮካዶ ችግኝ ደርሶ ፍሬ መስጠት በመጀመሩ ያገኙትን ምርት ከቤት ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም