በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠናክሮ ቀጥሏል
ሰቆጣ፤ ነሐሴ 2/2018 (ኢዜአ) ፦ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዜጎችን ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የአስተዳደሩ የሴቶች፣ ሕፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የወጣቶች ንቅናቄ ተሳትፎ ቡድን መሪ አቶ ሙሉጌታ ስኳር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዘንድሮው የክረምት ወራት 584 ሺህ 860 የሕብረተሰብ ክፍሎችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ወደ ሥራ መገባቱን አመልክተዋል።
እስካሁን በተደረገው ጥረትም ከ144 ሺህ በላይ ወጣቶችና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ 99 የአቅመ ደካሞችን ቤት በአዲስ መልክ መገንባት መቻሉን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ፣ የደም ልገሳ፣ የትምህርት ቁሳቁስ ማሰባሰብ፣ የአቅመ ደካሞችን ሰብል መዝራትና ሌሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም የዜጎች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የአንድነትና የትብብር እሴትን ይበልጥ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በሰቆጣ ወረዳ የሃሙሲት ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት ሃብታሙ ካሳ፤ በክረምቱ የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ መሳተፉን ነው የገለጸው።
በአሁኑ ወቅትም የአቅመ ደካሞችን ቤት ገንብተው ለማስረከብ እየሠሩ ሲሆን በችግኝ ተከላና የጽዳት ሥራዎችን ጨምሮ በሌሎች የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ላይ መሰማራታቸውን ገልጿል።
በሰቆጣ ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት ጥላሁን አበበ በበኩሉ፤ ከሌሎች በጎ ፈቃደኞች ጋር በመሆን የተማሪዎች መቀመጫ ወንበር በመጠገን ለአገልግሎት እንዲበቁ ማድረጋቸውን ተናግሯል።
የአቅመ ደካሞችን ቤት መጠገንን ጨምሮ በደም ልገሳና በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች በመሳተፍም የዜግነት ግዴታውን እየተወጣ እንደሚገኝ አስገንዝቧል።
በብሔረሰብ አስተዳደሩ በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ379 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ሥራዎችን በማከናወን ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ወደ ሥራ መገባቱ የሚታወስ ነው።