አረንጓዴ አሻራ ለትውልድ የሚተላለፍ ጠንካራ የአካባቢ ጥበቃ ባህል ነው - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴ አሻራ ለትውልድ የሚተላለፍ ጠንካራ የአካባቢ ጥበቃ ባህል ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2018 (ኢዜአ) ፦አረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያውያን ለትውልድ የሚያስተላልፉት ጠንካራ የአካባቢ ጥበቃ ባህል ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮርፖሬት አገልግሎት ኤክስኪዩቲቭ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሥራ ሃላፊዎችና ሠራተኞች፣ ’’ተስፋን እንትከል’’ በሚል መሪ ቃል በእንጦጦ ሸገር ፓርክ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ አከናውነዋል።
የባንኩ የኮርፖሬት አገልግሎት ኤክስኪዩቲቭ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ አረንጓዴ አሻራ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮችን መቋቋም ያስችላል።
በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ስራዎች የታዩ ተጨባጭ ለውጦች መኖራቸውን አንስተው፣ በተለይም ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
የተፈጥሮ ስነ ምህዳሯ የተጠበቀና አረንጓዴ አገርን ለቀጣይ ትውልድ ለማስረከብ ችግኝ መትከልና መንከባከብ ወሳኝ ሀገራዊ ሀላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ባንኩ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ250 ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል ማቀዱን ገልጸው፤አረንጓዴ አሻራ ለቀጣይ ትውልድ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ጠንካራ የኢትዮጵያዊያን የአካባቢ ጥበቃ ባህል መሆኑን ተናግረዋል።
የባንኩ አመራሮች እና ሰራተኞችም በዚህ ታላቅ ሀገራዊ መርሀግብር የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።