ቀጥታ፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሻለ ኑሮ ለመምራት አስችሎናል

ምዕራብ ሐረርጌ፤ ነሐሴ 2/2018 (ኢዜአ) ፦ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን በማቃለል  የተሻለ ኑሮ ለመምራት እንዳስቻላቸው በምዕራብ ሐረርጌ ዞን መሰላ እና ጭሮ ከተሞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ተናገሩ።

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በክረምት ወቅቱ እስካሁን ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መከናወኑን የዞኑ ገንዘብ ጽሕፈት ቤት ገልጿል።

በዞኑ የመሰላ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ፀዳለ እርገጤ እና አቶ ኢብራሂም ሙሜ፤ አቅም በማጣታቸው የተነሳ መኖሪያ ቤታቸውን መጠገን ተስኗቸው ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠው ነበር።


 

በአሁኑ ወቅት ግን በበጎ ፈቃድ ሥራው የመኖሪያ ቤታቸው በአዲስ መልክ ተገንብቶ የተሰጣቸው በመሆኑ እፎይታን ሰጥቶናል ብለዋል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተገነባላቸው መኖሪያ ቤት አዲስ ተስፋና ደስታ እንዳገኙ አመልክተው በአሁኑ ወቅት የተረጋጋ ኑሮ መምራት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በጭሮ ከተማ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወይዘሮ አይሻ ከድር፤ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ምቹ መኖሪያ ቤት እንደተገነባላቸውና የቤት ቁሳቁስ ድጋፍም እንዳገኙ ነው የሚናገሩት።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆኔ ማህበራዊ ችግሮችን በማቃለል የተሻለ ኑሮ ለመምራት አስችሎኛል ሲሉም ገልጸዋል።

የመሰላ ከተማ አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ አቶ ከድር አሊዪ በበኩላቸው፤ በክረምቱ ወቅት እየተካሄደ ባለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የ16 አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች የመኖሪያ ቤት ግንባታ መካሄዱን ተናግረዋል።


 

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ሕክምና የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች ከማሳከም ባለፈ 500 ደርዘን ደብተሮችን በመግዛት ለተማሪዎች ድጋፍ መደረጉን አመልክተዋል።

የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ገንዘብ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡሴይድ ሙአዘም በበኩላቸው፤ በዞኑ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ፣ የደም ልገሳን ጨምሮ በ18 ዘርፎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ ተከናውኗል ብለዋል።


 

ከእነዚህም የ40 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና የ70 ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታን ጨምሮ ከ4 ሺህ 800 በላይ የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤት ግንባታና ጥገና ስራ መከናወኑን አመልክተዋል።

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ የሕብረተሰቡን ተሳትፎ በማጠናከር ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ለማከናወን መታቀዱን አቶ ኡሴይድ ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም