ሀገራዊ ምክክሩ ለችግሮች መፍትሔ በማበጀት የተሻለች ሀገር ለመገንባት ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ለችግሮች መፍትሔ በማበጀት የተሻለች ሀገር ለመገንባት ያስችላል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2018 (ኢዜአ) ፦ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ለዘመናት ለዘለቁ ችግሮች መፍትሔ በማበጀት የተሻለች ሀገር ለመገንባት ዕድል እንደሚፈጥር ተመካካሪዎች ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።
በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ አራት ሺህ የሕዝብ ወኪሎች በስምንት ዐበይት አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ይገኛሉ።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተመካካሪዎች እንደተናገሩት ምክክሩ ለዘመናት ሲንከባለሉ የቆዩ ችግሮችን በመፍታት እና ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው እምነታቸውን ገልጸዋል።
ከተመካካሪዎች መካከል ሰይፈጀማል ሀጂ፤ በምክክሩ በሰከነ መንገድ በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን በመግለጽ ሀገራዊ ምክክሩ ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት ለዘላቂ ሰላም እና ልማት ትልቅ መሰረተ ይጥላል ብለዋል፡፡
ማንኛውንም ችግር በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት የስልጣኔ ምልክት መሆኑን ያስገነዘቡት ተመካካሪው፣ አሁን በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ምክክርም የዚህ አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላኛው ተመካካሪ መርዱ ገብረስላሴ በበኩላቸው፣ በምክክር የማይፈታ ችግር አይኖርም ብለዋል።
በመሆኑም ሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያውያንን አንድነት ይበልጥ በማጠናከር ልማት እና ብልጽግናን እንደሚያስቀጥል ትልቅ ተስፋ መሰነቃቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተውጣጡ ዜጎች የሚሳተፉበት አካታችነት ያለው መድረክ መሆኑ ለምክክር መድረኩ ልዩ ድምቀት እና ትክክለኛ የሀገሪቱን ምስል የሚያሳይ መሆኑን አንስተዋል።
ተመካካሪ ገበየሁ ደጎየ፤ የምክክር መድረኩ አሳታፊነት እጅግ አስደሳች መሆኑን ገልጸው፣ ይህ አካሄድ የኢትዮጵያውያንን አንድነት ለማጠናከር የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።
መድረኩ ለዘመናት ለቆዩ አለመግባባቶች ዘላቂ መፍትሔ በመስጠት ሁሉም ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር ምቹ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።