ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አገኘች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2018 (ኢዜአ)፦ በአሜሪካ ኦሬጎን እየተካሄደ ያለው 21ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዟል።

ማለዳ ላይ በተደረገው የ3000 ሜትር መሰናክል ሴቶች የፍጻሜ ውድድር  አትሌት አልማዝ ዮሐንስ 9 ደቂቃ ከ15 ሴኮንድ ከ81 ማይክሮ ሴኮንድ አንደኛ በመውጣት ለኢትዮጵያ በሻምፒዮናው የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታለች።

አትሌት ወሰኔ አሰፋ  9 ደቂቃ ከ30 ሴኮንድ ከ50 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ አግኝታለች።




ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ያስመዘገበቻቸውን ሜዳሊያዎች ብዛት ወደ አራት ከፍ አድርጋለች።

ኢትዮጵያ በአንድ የወርቅ፣ ሁለት የብር እና አንድ ነሐስ በድምሩ አራት ሜዳሊያዎችን በማግኘት በሜዳሊያ ሰንጠረዡ አራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

አሜሪካ፣ ኬንያ እና ቻይና በሜዳሊያ ሰንጠረዡ በቅደም ተከተል ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

ኢትዮጵያ ተጨማሪ ሜዳሊያ የምትጠብቅባቸው ውድድሮች ዛሬ እና ነገ ይደረጋሉ።

21ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ነገ ይጠናቀቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም