ቀጥታ፡

የኮሪደር ልማት ጤናማ አኗኗርና ፅዱ አካባቢን በመፍጠር ለጤናው ዘርፍ የላቀ ሚና አለው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2018 (ኢዜአ) ፦በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ጤናማ አኗኗርና ፅዱ አካባቢን በመፍጠር ለጤናው ዘርፍ ያለው አበርክቶ የላቀ መሆኑን የግሎባል ኮሌራ መቆጣጠሪያ ግብረ ኃይል የሀገር ድጋፍ መድረክ የቴክኒክ ባለሙያ ዶክተር ካትሪን ማክዌ ገለፁ።

ኢትዮጵያ የወረርሽኝ ዝግጁነትን በማጠናከር፣ የንፁህ ውሃ አቅርቦት፣ ንፅህናና ጤናማ አኗኗር ስርዓትን በማስፋት ለዓለም የጤና ስርዓት የበኩሏን እየተወጣች ነውም ብለዋል።

ዶክተር ካትሪን ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይም በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በኩል የወረርሽኝ ምላሽ የመስጠት አቅሙን በማጎልበት ረገድ ውጤታማ ተግባር አከናውኗል።


 

የክልል ጤና ቢሮዎች የወረርሽኝ ምላሽ ስርዓትን በመምራትና በየአካባቢያቸው ያለውን የበሽታ ሁኔታ የመከታተል አቅም እያደገ መምጣቱ የሚደነቅ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በኮሪደር ልማት እያከናወነች ያለችው ተግባር የጤናና የውሃ መሠረተ ልማትን ለማልማት እገዛ እንዳለውም ገልፀዋል።

ይህም የህብረተሰብ ጤናን ለመጠበቅና የንፅህናና ጤናማ አኗኗርን ማጠናከር የሚያስችል ነው ብለዋል።

የኮሪደር ልማት ስራ የወረርሽኞችን ስርጭት ለመቆጣጠርና በሽታዎችን ለመከላከል የሚያግዝ መሆኑንም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በሽታዎችን በመከላከል ረገድ ፈጠራ የታከለበት መንገድ በመከተል ውጤታማ ተግባር እያከናወነች መሆኑንም ተናግረዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ለበሽታዎች መንስዔና የወረርሽኞች ባህሪ እንዲቀያየር እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

ኢትዮጵያ የአየር ንብረትን ለመቋቋም እያከናወነች ያለው ተግባርና ቁርጠኛ አመራር በርካታ ትምህርት የሚወሰድበት መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ያላትን ልምድ ለሌሎች ሀገራት በማጋራት ተሞክሮዋን እንዲጠቀሙበት ማድረግ ይገባልም ብለዋል።

ውጤታማ የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ስራ የባለድርሻ አካላትን ትብብር የሚሻ በመሆኑ የመንግሥት ተቋማት፣ ለጋሾች እና የልማት አጋሮች በትብብር እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም