ቀጥታ፡

 የኢትዮጵያ የስንዴ ምርታማነት ዕድገት የአፍሪካን የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ የሚያስችል ተምሳሌታዊ ተሞክሮ ነው 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2018 (ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያ የስንዴ ምርታማነት ዕድገት የአፍሪካን የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ የሚያስችል ተምሳሌታዊ ተሞክሮ መሆኑን የቀድሞ የአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ የብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ አካባቢ ጉዳዮች ኮሚሽነር ጆሴ ፋል ሊዮኔል ኮሪያ ሳኩ ገለጹ። 

የአፍሪካ ሀገራትም የኢትዮጵያንና ሌሎች ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር በግብርናው መስክ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጥ የራስ አቅም መገንባት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ጆሴፋ ሊዮኔል ኮሪያ ሳኮ ለኢዜአ እንዳሉት፤ አፍሪካ ግብርናን ጨምሮ የምግብ ሉዓላዊነትንና የምርታማነት አቅምን የሚያጎለብት በርካታ የዕድገት ተስፋና ጸጋ የታደለች አህጉር ናት።

በዚህም የአፍሪካን እምቅ የዕድገትና የብልፅግና ተስፋዎች ወደ ዕድል በመቀየር የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የግብርና ምርታማነትን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።


 

የአህጉሪቷ የግብርና ምርታማነት እምቅ አቅምና ጸጋም የአፍሪካውያንን የምግብ ዋስትና በራስ አቅም በመሸፈን ከጥገኝነት መላቀቅ የሚያስችል የተቀናጀ ትብብርና ጥረት ማድረግን እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትም የአህጉሪቱን የእርስ በርስ ንግድ በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማጠናከር፣ ረሃብንና ድህነትን ለመቀነስ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

አፍሪካ ሙሉ በሙሉ በውጭ እርዳታ ላይ ከመመስረት ይልቅ የራሷን ሀብትና አቅም በመጠቀም ፕሮጀክቶችን በውጤታማነት ማከናወን እንደሚገባትም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነትና የአካባቢ ጥበቃ ስኬቶች ለአፍሪካ የዕድገት ተስፋ ተምሳሌት መሆናቸውን አብራርተዋል።

በተለይም በበጋ መስኖና በተለያዩ የመኸር ወቅቶች የስንዴ ምርታማነትን በማሳደግ፣ ከውጭ ምርት ጥገኝነት በመላቀቅ ለውጭ ንግድ የሚተርፍ አቅም መገንባቷ የሚደነቅ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አጠቃላይ የግብርና፣ የአካባቢ ጥበቃና የከተማ ልማት እመርታዊ ስኬቶችም የአፍሪካን የዕድገት ተስፋ ለመቅረጽ እንደ ልምድና ተሞክሮ ሊወሰዱ የሚችሉ መሆናቸውን አንስተዋል።


 

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርና በከተሞች መሠረተ ልማት ማዘመን ያከናወነቻቸው ተግባራትም ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከኢትዮጵያ ተሞክሮ ሊማሩና ሊጋሩት የሚገባ ወሳኝ የልማት አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራም የአካባቢ ሚዛንን ከመጠበቅ ባሻገር የኢትዮጵያን አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ለማሳለጥ አቅም እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

በዚህም የአፍሪካ ሀገራት በግብርና፣ በአካባቢ ጥበቃና በከተሞች ልማት ዘርፎች የተሳኩ ተሞክሮዎችን በመለዋወጥና በተቀናጀ መንገድ በመስራት የአህጉሪቱን ዘላቂ ዕድገት ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም