ቀጥታ፡

በአማራ ክልል በመኸር እርሻ 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል

ባህር ዳር፤ ነሐሴ 2/2018 (ኢዜአ) ፦በአማራ ክልል በመኸር እርሻ 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።

በቢሮው የሰብል ልማት ማስፋፊያ ባለሙያ ወይዘሮ እንየ አሰፋ እንደገለጹት፤ በተያዘው የክረምት ወቅት የመኸር እርሻ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።

በዚህም እስካሁን ከ5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር በመሸፈን የእቅዱን 91 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።

እቅዱን ሙሉ ለሙሉ ለማሳካትም ጤፍ፣ ሽንብራና ሌሎች ፈጥነው የሚደርሱ ሰብሎችን በመዝራት በአጠቃላይ 205 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። 

ከዚህ ውስጥ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም የለማ ሲሆን በመስመር መዝራትና ሌሎች አዳዲስ አሰራሮች መተግበራቸውንም አስረድተዋል።

በተጨማሪም ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ እስካሁን ጥቅም ላይ መዋሉን አረጋግጠዋል።

በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ ቋር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ወንድምሁነኝ ዘለቀ እንደገለጹት፤ በክረምቱ አንድ ሄክታር ተኩል መሬታቸውን በሩዝ ሰብል በመሸፈን የመንከባከብ ስራ እየሰሩ ይገኛሉ።

ምርታማነቱን ለማሳደግም 2 ኩንታል ማዳበሪያ ተጠቅመው መዝራታቸውን ጠቁመው፣ ከዘሩት ማሳ ላይ 75 ኩንታል የሩዝ ምርት ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በባህር ዳር ከተማ ዘንዘልማ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ከፍያለው ንጉሴ በበኩላቸው፤ ለመኸር እርሻ አስፈላጊ ግብአቶችን በማግኘታቸው ከ5 ሄክታር በላይ በሆነ መሬታቸው ሩዝ፣ ዳጉሳ፣ ማሽላና ጤፍ ማልማታቸውን ተናግረዋል።

ከዚህም ከ130 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁ ነው የተናገሩት።

በክረምቱ ወቅት እየተካሄደ ባለው የሰብል ልማት ስራ ከአራት ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም