የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምክንያታዊና ፍትኃዊ የውሃ ሀብት አጠቃቀምን መሰረት ያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምክንያታዊና ፍትኃዊ የውሃ ሀብት አጠቃቀምን መሰረት ያደረገ ነው
አርባ ምንጭ፤ ነሐሴ 2/2018 (ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምክንያታዊና ፍትኃዊ የውሃ ሀብት አጠቃቀምን መሰረት ያደረገ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የግብጽን ሴራና ተጽዕኖ በመቋቋም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን እንዳሳኩት ሁሉ የባህር በር ባለቤትነትም ተገቢ ምላሽ እንዲያገኝ የጋራ አቋም ይዘው ለማሳካት እየተንቀሳቀሱ ነው።
ኢዜአ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ለሀገር ሁለንተናዊ የዕድገት መሰረት እንደሆነ ተናግረዋል።
ከምሁራኑ መካከል በዩኒቨርሲቲው የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የውሃ ሀብት ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ኤልያስ ገበየሁ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብት አልምታ የመጠቀም መብት አላት።
ስታራምደው የነበረው በፍትሃዊነት ላይ የተመሰረተ የውሃ ሃብት አጠቃቀምና በጋራ የመልማት ጽኑ አቋምም ሁሉን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ይሁንና በውሃ ሀብቷን በፍትሃዊነት እንዳትጠቀም በተለያዩ አካላት በተለይ በግብጽ በተለያየ መንገድ ጫና ሲደረግባት መቆየቱን ኤልያስ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
በዚህም የቅኝ ግዛት የውሃ ስምምነቶችን መሰረት በማድረግ ግብጽ በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ ለዘመናት የነበራትን የበላይነት ለማስቀጠል ከነበራት ጽኑ ፍላጎት የሕዳሴው ግድብ እንዳይገነባ ከጅምሩ አንስቶ ለማስተጓጎል ስትጥር ቆይታለች።
ይህን የግብጽ ሴራ በማክሸፍ ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን አልምታ በፍትሀዊነት እንድትጠቀም መንግስትና ህዝብ በተባበረ ክንድ ባከናወኑት ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራ እና ለግንባታው ባሳዩት ቁርጠኝነት ሴራውን በማክሸፍ ግድቡን እውን ማድረግ ተችሏል።
በዚህም ኢትዮጵያ በውሃ ሀብቷ የመልማት መብቷን በተግባር ማረጋገጧን የገለጹት ምሁሩ፣ አሁንም ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት እንዳትሆን ግብጽ በተለያየ መንገድ እያሴረች መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣናው ሀገራት በትብብር የመልማት መርህን ወደጎን ያለውና በግብጽ ሴራ ጭምር ከቀይ ባሕር እንድንርቅ የተደረገበት ይህ እኩይ ተግባር የኢትዮጵያን ታሪካዊና ሕጋዊ መብት የጣሰ መሆኑንም አንስተዋል።
በታሪክም ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት የነበረችና ከቀይ ባህር ጋር የነበራት ትስስርም የቆየ እንደሆነ ምሁሩ አመልክተዋል።
ምሁሩ አክለውም ኢትዮጵያውያን በባህር በር ላይ የጀመሩትን የጋራ አቋም ካጠናከሩ ይህን ሴራዋን ማክሸፍ ይቻላል ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው መምህርና በውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የውሃ ሀብት እና ምህንድስና ፋካልቲ ተመራማሪ ሳሙኤል ዳጋሎ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ከዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያን ያገለለውና የውሃ ሀብቷን እንዳትጠቀም በሴራ የተዘጋጁ የቅኝ ግዛት ውሎች የአንድ ወገን ተጠቃሚነትን ብቻ ያረጋገጡ መሆናቸውን አንስተዋል።
ሁሌም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በተጻራሪ የምትቆመው ግብጽ ዛሬም ኢትዮጵያ የባህር በር እንደተቆለፈባት እንድትኖር ብርቱ ጥረት እያደረገች መሆኗን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለዘመናት የባሕር በር ባለቤት መሆኗን አስታውሰው፤ ለኢትዮጵያ የባሕር በር የህልውና ጉዳይና የሕዝብ ጥያቄ መሆኑን አስረድተዋል።
ይሁንና ዛሬም ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ አዙሪት ያልወጣችው ግብፅ በሕዳሴው ግድብ ያላሳካችውን ሴራ በቀይ ባህር ለማሳካት እያካሄደች ያለው ዘመቻ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለድርድር እንደማይቀርብና ከዓለም አቀፍ ደኅንነት ጋር ጭምር እንደሚገናኝ ምሁሩ አያይዘው ገልጸዋል።