ቀጥታ፡

ኦሮሞ በታሪኩ የተቃወመው የተበላሸ አስተዳደርን እንጂ ኢትዮጵያን አይደለም - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 1/2018 (ኢዜአ) ፦ የኦሮሞ ሕዝብ በታሪኩ የተቃወመው የተበላሸ የአስተዳደር ሥርዓትን እንጂ ኢትዮጵያን አይደለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (OBN) ጋር ቆይታ አድርገዋል።

የኦሮሞ ሕዝብ በታሪኩ የተቃወመው የተበላሸ የአስተዳደር ሥርዓትን እንጂ ሀገርን (ኢትዮጵያን) አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሀገርን በመገንባት ሂደትም ደሙን፣ አጥንቱን እና ላቡን ማፍሰሱን ገልጸዋል።

የኦሮሞ ሕዝብ የትግል ጥያቄዎች በዋናነት በሦስት መሠረታዊ ክፍሎች የሚከፈሉ መሆኑን እና እነዚህም የኢኮኖሚ፣ የማንነት እና የዴሞክራሲ ጥያቄ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢኮኖሚ ጥያቄን በተመለከተ እንደገለጹት ህዝቡ የመሬት እና የሀብት ባለቤት የመሆን፣ በላቡ ሠርቶ የማደግ እና አካባቢውን የመቀየር ፍላጎት እንደነበረው ጠቁመዋል።

መሬት ለኦሮሞ ሕይወቱ ቢሆንም፣ ይህ ሀብቱ ሲነጠቅ እና ሲበዘበዝ መቆየቱ እንዲሁም አራሹ አርሶ አምርቶ የመጠቀም መብት ማጣቱ ዋነኛ የትግል መነሻ ሆኗል ነው ያሉት።

የማንነት ጥያቄን በተመለከተ ደግሞ ይህ ጥያቄ አፋን ኦሮሞን ከመናገር ባለፈ ባህልን፣ ማንነትን፣ ሥነ-ምግባርን (ሰፉ) ታላላቆችን፣ ፍጥረታትን እና ፈጣሪን ማክበርን በውስጡ ያካተተ ጥልቅ ጥያቄ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

 

በኦሮሞነት ማንነት አድጎ ቋንቋን መናገር ብቻውን የማንነት ጥያቄን ሙሉ በሙሉ ይመልሳል ማለት አይቻልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ስለዚህ የቋንቋ፣ የባህል እና የማንነት ጥያቄዎች አሁንም እንዳሉ ጠቁመዋል።

ከዴሞክራሲ ጥያቄ አንጻር ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ የራሱ የሆነ አሳታፊ የገዳ ሥርዓት የነበረው ሕዝብ በመሆኑ፣ ራሱን በራሱ የማስተዳደር፣ የራሱን ሕግ የማውጣት እና በሕጉ የመተዳደር የረጅም ጊዜ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ እንደነበረው ጠቁመዋል።

የመንግሥት አስተዳደር ደግሞ ሕዝቡ ከለመደው ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር አንፃር ተቃራኒ ሲሆንም ጥያቄዎችን ሲያነሣ እንደነበርም ገልጸዋል።

ይህ የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ቢቆይም፣ በሚፈለገው ፍጥነት ድል ሳያመጣ የዘገየባቸውን ምክንያቶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአራት ዋና ዋና ነጥቦች አስቀምጠዋል።

አንደኛው የስትራቴጂያዊ ሐሳብ እጥረት ነው ሲሆን ምርት ለማግኘት ትራክተር ቢኖርም 'ምርጥ ዘር' ከሌለ ዋጋ እንደሌለው ሁሉ፣ የትግል ግብን ለማሳካት የሚያስችል ጥራት ያለው ስትራቴጂያዊ ሐሳብ አለመኖር ትልቁ ክፍተት ነበር ሲሉ በምሳሌ አስረድተዋል።

 

ሁለተኛው የአንድነት እጥረት ነው መሆኑን ጠቅሰው ኦሮሞ በሰፊ መሬት ላይ የሚኖር እና የጋራ ማንነት ያለው ቢሆንም፣ በፖለቲካ ሴራዎች፣ በእምነት፣ በወንዝ እና በዞን በመከፋፈል ጠንካራ ውስጣዊ አንድነትን ማስቀጠል አለመቻሉን አንስተዋል።

ሦስተኛ የግንኙነት አያያዝ ችግር እንደሆነ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሌሎች ኃይሎች ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶች በጊዜያዊ ፍላጎት ላይ ብቻ የተመሠረቱ መሆናቸውና የኦሮሞን ሕዝብ ፍላጎት ከማስከበር ይልቅ ለሌሎች ተገዢ ወይም አገልጋይ የሚያደርጉ በመሆናቸው በሂደቱ ላይ ትልቅ ጉዳት አምጥቷል ብለዋል።

አራተኛው የአመራር እጦት እና የአሸናፊነት ሥነ-ልቦና ማጣት መሆኑን ገልጸዋል።

ሕዝቡን አደራጅቶ እና አቅጣጫ አስይዞ ሊመራ የሚችል ትልቅ ዕይታ ያለው አመራር ማጣት እንቅፋት እንደነበር አንሥተዋል።

ትግሉን ለማሸነፍ ልክ እንደ አንበሳ የአሸናፊነት አስተሳሰብ ይዞ መነሣት ሲገባው፣ ገና ከመጀመሪያው የመሸነፍ ስጋት ውስጥ መግባት የድል እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም