ቀጥታ፡

የኦሮሞ ሕዝብ የዘመናት የማንነትና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች በአሁኑ ወቅት ምላሽ እያገኙ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 1/2018 (ኢዜአ)፦ የኦሮሞ ሕዝብ የዘመናት የማንነትና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች በአሁኑ ወቅት ምላሽ እያገኙ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (OBN) ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኦሮሞ ሕዝብ የዘመናት የትግል መነሻ ከሆኑት ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል የኢኮኖሚ፣ የማንነት እና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች እንደሚጠቀስ ገልጸዋል።

በተለይም የመሬት ባለቤትነት አለመከበር እና ማንነትን በአግባቡ ማንጸባረቅ አለመቻል ለትግሉ መነሻ እንደነበሩ ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት ግን እነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ እያገኙ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ሕዝቡ ላለፉት ዘመናት ያደረገው ትግል የሚፈለገውን ውጤት ሳያመጣ የቆየው አንድነቱን ማጠናከር ባለመቻሉ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተለያዩ ጊዜያት በሃይማኖት፣ በአካባቢ፣ በዞን እና በመንደር የመከፋፈል ሁኔታዎች ይታዩ እንደነበር አንስተዋል።

በተጨማሪም አቻ ካልሆኑ አካላት ጋር የተደረጉ አላስፈላጊ ጥምረቶች ለትግሉ ውጤታማ አለመሆን ምክንያት መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

የሕዝቡ ትግል የሚፈለገውን ውጤት እንዳያመጣ ያደረገው ዋናው ምክንያት የአመራር ችግር መሆኑን አመልክተዋል።

አመራሩ ትልቅ እና አሸናፊ ሃሳብ ይዞ ወደ ተግባር ካልገባ ውጤት ማምጣት እንደማይቻል ገልጸዋል።

በሌላ በኩል፣ የኦሮሞ ሕዝብ በየትኛውም ዘመን ቢሆን የታገለው ጨቋኝ ስርዓትን እንጂ ኢትዮጵያን ታግሎ እንደማያውቅ እና ሀገሩን ለመክዳት ያሰበበት አንድም ጊዜ እንደሌለ ገልጸዋል።

የኦሮሞ ህዝብ ለኢትዮጵያ ግንባታ ብዙ ዋጋ የከፈለ ህዝብ እንደሆነም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም