ቀጥታ፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አግልግሎቶች እንዲሳለጡ እያገዘ ነው

ጎንደር፤ ነሐሴ 1/2018 (ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን ለማሳለጥ ማገዙን የዞኑ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ።

የጠዳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአቅመ ደካሞችን ቤት ለመገንባት የሚውል 115 ኩንታል ሲሚንቶ ዛሬ በድጋፍ አበርክቷል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ቀኑ ቢያድጎ በድጋፍ መርሀግብሩ ላይ  እንደገለጹት፣ በዞኑ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 830 ሺህ ወጣቶችን ያሳተፈ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

አገልግሎቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን ለማሳለጥ እያገዘ መሆኑንም ገልጸዋል።

በበጎ አገልግሎቱ ወጣቶችንና ተቋማትን በማሳተፍ ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ከመርዳት ባለፈ እርስ በርስ የመረዳዳት ባህልን ለማዳበር መሰራቱንም ጠቁመዋል። 

በዚህም በክረምቱ እስካሁን ድረስ 652 የአቅመ ደካሞች ቤት በአዲስ በመስራትና በመጠገን፣ ከ9 ሺህ ለሚበልጡተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት የመስጠት እንዲሁም  ከ11 ሺህ ደርዘን በላይ ደብተር ማሰባሰብ ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።

ተቋማትና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን አንስተው የዛሬው ድጋፍም የዚሁ አካል ነው ብለዋል።


 

የጠዳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን አቶ ዘመነ ሀብቱ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ ኮሌጁ በበጎ ፈቃድ አገልገሎት በንቃት በመሳተፍ የማህበራዊ ሃላፊነቱን ከመወጣት ባለፈ የመረዳዳት ባህልን እያጎለበተ መሆኑን ተናግረዋል። 

በአሁኑ ወቅትም ኮሌጁ የአቅመ ደካሞችን ቤት ለመገንባት እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ 115 ኩንታል ሲሚንቶ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

ኮሌጁ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር እንዲጠናከር የጀመረውን ድጋፍ በቀጣይም አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም