የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ያስመዘገበውን ለውጥ ማጠናከር ይገባል - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ - ኢዜአ አማርኛ
የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ያስመዘገበውን ለውጥ ማጠናከር ይገባል - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 1/2018 (ኢዜአ)፦ የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ያስመዘገበውን ለውጥ ማጠናከር እንደሚገባ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ስር እየተካሄዱ ያሉ የአዳማ ጋርመንትና ኢንዱስትሪ፣ የጋሻ የሠራዊቱ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክት እና የመከላከያ ባጅና ሜዳሊያ ማምረቻ ፋብሪካን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የአዳማ ጋርመንት ኢንዱስትሪ ያስገነባውን አዲስ የማስፋፊያና የማሻሻያ ፕሮጀክት መርቀው ከፍተዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በጉብኝታቸው ወቅት፣ የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን አመራሮችና ሠራተኞች ላስመዘገቡት ውጤት በማመስገን የተገኘው ለውጥ ሳያዘናጋቸው ለበለጠ ውጤት እንዲተጉ አሳስበዋል።
በቀጣይም የምርት ጥራትን በማሻሻል፣ የምርምርና የቴክኖሎጂ ልማትን በማስፋፋት፣ የዲጂታላይዜሽን ሥራዎችን በማጠናከር፣ የግብዓት አቅርቦትን በራስ አቅም በማሳደግ በአፍሪካ ደረጃ ተወዳዳሪ ኢንዱስትሪ እንዲገነባ አቅጣጫ ሰጥተዋል።
ሠራዊቱ መለኪያው ሀገሩ ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን የተቋሙንና የሀገራችንን ፍላጎት በማሳካት ያለውን ሚና ይበልጥ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
በጉብኝቱ ላይ የአዳማ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች እና የፋውንዴሽኑ የሥራ ኃላፊዎች መገኘታቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ መረጃ አመላክቷል።