በሲዳማ ክልል የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለኢንዱስትሪ ልማት መስፋፋት ምቹ መደላድል ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለኢንዱስትሪ ልማት መስፋፋት ምቹ መደላድል ፈጥሯል
ሃዋሳ፣ ነሀሴ1/2018(ኢዜአ)፡-በሲዳማ ክልል የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለኢንዱስትሪ ልማት መስፋፋት ምቹ መደላድል መፍጠሩን የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አብርሃም ማርሻሎ ገለጹ።
የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የ2018 በጀት አመት አፈጻጸምና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በሃዋሳ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አብርሃም ማርሻሎ እንደገለጹት በክልሉ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለኢንዱስትሪ ልማት መስፋፋት ምቹ መደላድል ፈጥሯል።
ይህም የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በማሳደግ ለዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የመተካት አቅምን እያሳደገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቀጣይም የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ይበልጥ ለማሳደግ መስረተ ልማቶችን በቅንጅት የማሟላት ሥራው በቀጣይም ይጠናከራል ብለዋል።
የክልሉ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ አሻግሬ ጀምበሬ በበኩላቸው በክልሉ የኢንዱስትሪ አቅምን በማጠናከር የማምረት አቅምን የማሳደግ፣ የስራ ዕድል የመፍጠር፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን መጠን የመጨመርና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የመተካት ሥራ በትኩረት መከናወኑን ጠቁመዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ249 በላይ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ የማስገባትና ነባሮቹን በመደገፍ ከ22 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንም ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ ከክልሉ 14 ሺህ 500 ቶን የኢንዱስትሪ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ 155 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱንም አቶ አሻግሬ ጠቅሰዋል።
በተመሳሳይ 290 ሚሊዮን ዶላር የሚገመቱ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ተችሏል ብለዋል።