ቀጥታ፡

የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማሳደግ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ወሳኝ ሚና አለው

ድሬዳዋ፣ ነሐሴ 1/2018(ኢዜአ)፡-የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማሳደግ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ወሳኝ ሚና እንዳለው የብልጽግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ተናገሩ።

ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ "የወጣቶች የሥራ ፈጣሪነት ባህል ለብልፅግና ስኬት" በሚል አብይ ርዕሰ በአደረጃጀቶች ለታቀፉ ወጣቶች ዛሬ ስልጠና ሰጥቷል።


 

በስልጠናው ላይ አቶ ኢብራሒም ዩሱፍ እንዳሉት፤ የወጣቶችን ሁለንተናዊ አገራዊ ተሳትፎ ማሳደግ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት እየተደረገ ባለው ጥረት ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

ለዚህም  የወጣቶችን  ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚና ፖለቲካ አቅማቸውን ለመገንባት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም የሥራ ባህልንና ተወዳዳሪነት በማሳደግ ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት የሚያበረክቱበትን ተደማሪ አቅም ለመፍጠር እንደሚያግዝ  ገልጸዋል።

የወጣቱን አቅም ዛሬ በመገንባት ነገ ሀገር ተረካቢ ኃይል ማድረግ እንደሚገባ ገልጸው፣ አስተዳደሩም ይህን እውን ለማድረግ   በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በወጣቱ ላይ የሚፈለገው ለውጥ እና ውጤት እንዲመጣ ዛሬ የተሰጠው ስልጠና ወሳኝ አበርክቶ እንደሚኖረውም ገልጸዋል።


 

የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን የወጣቶች ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ በሐር አብደላ በበኩላቸው እንዳሉት  ወጣቶች በአስተዳደሩ ለተጀመሩ ሁለንተናዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ስኬታማነት በቁርጠኝነት እየተጉ ይገኛሉ።

በገጠርና በከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች በሙሉ የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በዘንድሮ ክረምት በ14 የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች 300 ሺህ የሚጠጉ ወጣቶች ተሳትፈው ውጤታማ የልማት ተግባራት በማከናወን ላይ ይገኛሉ ሲሉም አክለዋል።

ከስልጠና ተሳታፊ ወጣቶች መካከል ወጣት አሮን ሙሴ እና ሐምዲያ መሐመድ ስልጠናው የወጣቱን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነትና የልማት ተሳትፎ ለማጠናከር  የተሻለ ዕድል  የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም