ቀጥታ፡

በሲዳማ ክልል አርሶ አደሩን ከእንስሳት ልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ሆነዋል

ይርጋለም፤ ነሀሴ 1/2018 (ኢዜአ)፡-አርሶ አደሩን ከእንስሳት ልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ በመኖ አቅርቦትና ጤና አጠባበቅ ላይ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን የሲዳማ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አብርሀም ማርሻሎ ተናገሩ።

የሲዳማ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ የ2019 በጀት ዓመት የእንስሳት መኖ ልማትና የበሽታ መከላከያ ክትባት ሥራዎች ይፋዊ ማስጀመሪያ መርሀግብር በይርጋዓለም ከተማ ተካሂዷል።


 

‎በመርሀግብሩ ላይ የሲዳማ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አብርሀም ማርሻሎ በክልሉ  የአርሶ አደሩን ከእንስሳት ልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ የመኖ አቅርቦትና ጤና አጠባበቅ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ዘመናዊ የእንስሳት እርባታ ዘዴው ‎ለእንስሳት ዝርያ ማሻሻል፣ ለመኖ አቅርቦትና ለጤና አጠባበቅ ሥራ ከፍተኛ እገዛ ማድረጉንም ገልጸዋል።

‎አርሶ አደሩ የመኖ አቅርቦቱን ከሌማት ቱሩፋት ሥራ ጋር በማቀናጀትና የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን በመጠቀም ምርታማነቱን ማሳደጉን ጠቁመዋል።

የክልሉ መንግስት የአርሶ አደሩን ከእንስሳት ልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ከሚያደርገው ሞያዊ እገዛ በተጨማሪ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን ማቅረቡን አንስተዋል።


 

የክልሉ እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰፋ ፎና በክልሉ የሌማት ትሩፋት መርሀግብር ከመጀመሩ በፊት 170 ሺህ የነበረው የተሻሻሉ የዳልጋ ከብቶች ቁጥር በአሁኑ ወቅት ወደ 600 ሺህ ለማሳደግ መቻሉን አብራርተዋል።

ይህም የክልሉን የእንስሳትና እንስሳት ተዋጽኦ ከማሳደግ ባለፈ የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት መሳደጉን አንስተዋል።

ከዚህ በተጓዳኝም የእንስሳት መኖ አቅርቦትን ለማስፋት በተደረገ ጥረት በበጀት ዓመቱ ከ32 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ  ልማቱ መካሄዱን  ጠቁመዋል።

በክልሉ የእንስሳት ጤናን ለመጠበቅም የበሽታ መከላከልና ክትባት ሽፋኑንለማሳደግ በቅንጅት መሰራቱን  አስረድተዋል።

ይህም የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ለማሳካትና  የአርሶ አደሩ  ተጠቃሚነት ከማሳድግ ባለፈ ለኢንዱስትሪዎች  ግብአት ለማቅረብ  አስችሏል ብለዋል።


 

በይርጋዓለም ከተማ ጋኔ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ደረጀ ሙጤ የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው የወተት ላሞች በማርባት  ወተትና የወተት ተዋጾን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለእንስሳቱም በግማሽ ሄክታር መሬታቸው ላይ የመኖ ሣር በማልማት  ውጤታማነታቸውን ለማጉላት  እየሰሩ መሆናቸውን  ተናግረዋል።

‎የእንስሳቱን ምርታማነት ለማሳደግ የምጥን መኖ አቅርቦትና  ጤናቸውን  መከታተል ላይ የባለሞያ ድጋፍ ማግኘታቸውንም ጠቁመዋል።


 

በማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ ላይ የሲዳማ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደን ጨምሮ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን በይርጋለም ከተማም የተለያዩ የሌማት ትሩፋት ስራዎች ተጎብኝተዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም