የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዘመናዊ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት አቅም ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዘመናዊ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት አቅም ፈጥሯል
ወልቂጤ፤ ነሐሴ1/2018 (ኢዜአ):-የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዘመናዊ የሕክምና አገልግሎት ለህብረተሰቡ የፈውስ ሕክምናን በተሻለ ለመስጠት አቅም መፍጠሩን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሥራ እንቅስቃሴን ተመልክተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ከምልከታው በኋላ ከሆስፒታሉ አመራሮችና ሠራተኞች ጋር ባደረጉት ውይይት እንደተናገሩት፤ የሆስፒታሉ ዘመናዊ ሕህክምና አገልግሎት ለህብረተሰቡን የፈውስ ሕክምናን በተሻለ ለመስጠት አቅም ፈጥሯል።
ሆስፒታሉ የሚሰጣቸውን የሕክምና አገልግሎቶች በማስፋት የህብረተሰቡን እንግልት ማስቀረት መቻሉንም ጠቁመዋል።
የሆስፒታሉን ምድረ ግቢ ሳቢ ለማድረግና የአገልግሎት አሰጣጡን ፈጣንና ውጤታማ ለማድረግ የተዘረጋው ከወረቀት ንኪኪ ነፃ የሆነ አሰራርም አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አብድልሙህሲን ሀሰን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የዩኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጥራቱን የጠበቀ ተግባር ተኮር ትምህርት በመስጠት ብቁ የጤና ባለሙያዎችን እያፈራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ኮምፕርሄንሲቭ ሆስፒታሉም በተለያዩ የስፔሻሊስት ሕክምና ዘርፎች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።
ይህም ህብረተሰቡ የተሻለ የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ይደርስበት የነበረውን እንግልትና ተጨማሪ ወጪ ማስቀረቱን ነው የገለጹት።
በአሁኑ ወቅት ሆስፒታሉ ዘመናዊ ሕክምና መስጠት የሚያስችለውን አቅም ገንብቷል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በቀጣይም ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት መስጠቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በውይይቱም የኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና የሆስፒታሉ ሠራተኞች እንዲሁም የክልሉ እና የዞኖች ሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡