የጤና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አነስተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች እፎይታን እየሰጠ ነው - የጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የጤና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አነስተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች እፎይታን እየሰጠ ነው - የጤና ሚኒስቴር
ባህር ዳር ፤ነሐሴ 1/2018 (ኢዜአ):--የጤና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አነስተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች እፎይታን እየሰጠ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅዳስ ዳባ ገለፁ።
ሚኒስትሯና ሌሎች አመራሮች በተገኙበት የጤና የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ ሥራዎች በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል።
ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ የጤና በጎ ፈቃድ አገልግሎት አነስተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች እፎታን እየሰጠ ነው።
በጤና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ20 ሚሊዮን የሚበልጡ ወገኖችን ነፃ የሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህም ከበጎ ፈቃደኞች ደም የመሰብሰብ፣ የሕክምና መሳሪያዎችን የመጠገን፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ፣ የመኖሪያ ቤት ጥገናና ግንባታ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
በዛሬው እለትም በባህር ዳር ቁልቋል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለ500 ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍና የቅድመ አንደኛ ደረጃ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ ሥራ መጀመሩን ገልፀዋል።
አነስተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች የመኖሪያ ቤት እድሳትና ግንባታ ሥራ መጀመሩን ጠቅሰው፣ ተግባራቱ ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብልዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግስቱ በበኩላቸው፤ በጤናው ዘርፍ የሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ ስራዎች የማህበረሰቡ ችግር በሚቃልል መንገድ ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
በተለይም የበርካታ ወገኖችን ሕይወት የሚታደገውን ከበጎ ፈቃደኞች ደም የመሰብሰብ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በባህር ዳር ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት እየተከናወነ ያለው የደም አሰባሰብ ሥራ ለሌሎች ምሳሌ ነው ብለዋል።
የበጎ ፈቃድ ሥራዎች የባህር ዳር ከተማን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማሳደግ ከፍተኛ ድርሻ ማበርከታቸውን የገለጹት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ ናቸው።
በበጎ ፈቃድ ስራው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ፣ ደጋፊ ለሌላቸው ወገኖች የቤት እድሳትና ጥገና፣ የትምህርት ቁሳቁስ ማሰባሰብን ጨምሮ በ17 የልማት ተግባራት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የጤና ሚኒስቴር በከተማው ያደረገው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ፣ የቤት እድሳትና ግንባታ እንዲሁም ሌሎች የበጎ ፈቃድ ሥራዎች የዚሁ ማሳያ ናቸው ሲሉም ጠቁመዋል።
በሚኒስቴሩ የቤት ግንባታቸው የተጀመረላቸው እማሆይ ጥሩ ብርሌ በበኩላቸው፤ መኖሪያ ቤታቸው በአገልግሎት ብዛት በማርጀቱ ለዝናብና ለጸሀይ በማጋለጥ ሲቸገሩ መቆየታቸውን አንስተዋል።
በዛሬው እለት የተጀመረው የቤቱ እድሳት ከችግሩ እንደሚገላግላቸው ተስፋቸውን ገልፀዋል።