ቀጥታ፡

የደጃዝማች በላይ ዘለቀ አውሮፕላን ማረፊያ አዲስ ተርሚናል የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ፍሰቱን ያቀላጥፋል

ባህር ዳር ፤ነሐሴ 1/2018(ኢዜአ)፡- የደጃዝማች በላይ ዘለቀ አውሮፕላን ማረፊያ አዲስ ተርሚናል የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ፍሰቱን እንደሚያቀላጥፍ በዘርፉ የተሰማሩ ግለሰቦች ገለጹ።

በባህር ዳር ከተማ የደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአዲስ የተገነባውን ተርሚናል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መመረቃቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ በባህር ዳር የተገነባው ተርሚናል በኢትዮጵያ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቀጥሎ ግዙፉ ተርሚናል መሆኑን መግለጻቸው አይዘነጋም። 

አስተያየት ሰጪዎች እንዳሉት የአውሮፕላን ማረፊያው ተርሚናል በአዲስ መልክ መገንባቱ የከተማዋን የቱሪዝም፣ የኢንቨስትመንትና የንግድ እንቅስቃሴ ለማፋጠን ያስችላል ብለዋል።

የባህር ዳር አስጎብኚዎች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ማስተዋል ዘለቀ እንደገለጹት፤ የተርሚናሉ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ መገንባት የቱሪዝም ዘርፉን ዕድገት የሚያፋጥን ነው። 

ባህር ዳር በጣና ሐይቅ የሚገኙ ገዳማትን፣ የጢስ አባይ ፏፏቴንና ሌሎች በውስጧ የሚገኙ የመስህብ ሀብቶችን ለመጎብኘት የሚመጡ እንግዶችን በማስተናገድ የምትታወቅ ከተማ መሆኗን ገልጸዋል። 

በተጨማሪም ወደ ጎንደር፣ ላሊበላና ሌሎች የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች ለመጓዝ ለሚመጡ የውጭና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ዋነኛ መተላለፊያ በመሆን እያገለገለች ትገኛለች ብለዋል። 

ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ተርሚናል መገንባቱም ወደ ከተማዋ የሚመጡ ቱሪስቶችን ምቾትና ደህንነት በመጠበቅ የሀገራችንን ገጽታ ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላው በአስጎብኚነት ሥራ የተሰማሩት አቶ አበበ ያረጋል በበኩላቸው፤ ግዙፍና ዘመናዊ ተደርጎ የተገነባው ተርሚናሉ፤ ወደ አካባቢው የሚመጡ ቱሪስቶችን ያለምንም መጨናነቅና እንግልት ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል። 

ይህም በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሀብቶችን በስፋት በመሳብ ከተማዋን ይበልጥ ለማዘመን እንደሚያግዝም አስረድተዋል።

ተርሚናሉ ደረጃውን ጠብቆ መገንባቱ ለጎብኚዎች ፈጣን አገልግሎት በመስጠት የከተማዋን የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ያቀላጥፋል ያሉት ደግሞ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጋሻው እንዳለው ናቸው። 


 

የተፈጥሮ፣ ሰው ሰራሽና ታሪካዊ ቅርሶች ባለቤት የሆነችውን የባህርዳር ከተማ በኮሪደርና በአረንጓዴ ልማት፣ በሰፋፊ የአስፋልት መንገዶችና በአዲሱ የአባይ ድልድይ ግንባታ በማጀብ ተመራጭ መዳረሻ እንድትሆን መደረጉን አመልክተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመረቀው አዲሱ ተርሚናል መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ማሳያ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ በቀጣይም ዘመናዊ ሎጆችና ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ግንባታ ላይ ማተኮር ይገባል ብለዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም