በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 664 ሺህ 505 አዳዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 664 ሺህ 505 አዳዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 1/2018 (ኢዜአ)፦በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 664 ሺህ 505 አዳዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው ገለጹ።
የአገልግሎቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው የአገልግሎቱ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅዱ ዙሪያ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው በመግለጫቸው አገልግሎቱ በበጀት ዓመቱ ውጤታማ ተግባራት ማከናወኑን ጠቁመው፤ በዚህም የደንበኞቹን ቁጥርም 5 ነጥብ 88 ሚሊየን ማድረሱን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ 664 ሺህ 505 አዳዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉንና ከዕቅድ አንጻር 83 ነጥብ 1 በመቶ መከናወኑን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ 205 የገጠር ቀበሌዎችንና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ዋና ስራ አስፈጻሚው ጨምረው አስታውቀዋል።
በበጀት ዓመቱ 118 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ለደንበኞች ከቀረበ የኤሌክትሪክ ሀይል ሽያጭ መሰብሰቡንና ከዕቅድ አንጻርም 102 ነጥብ 6 በመቶ ማሳካት መቻሉን አንስተዋል።
በኤሌክትሪክ ሀይል ማሰራጫ መስመር መሰረተ ልማት ዝርጋታና ጥገና ላይም ሰፊ ስራ መሰራቱን ጠቁመው በዚህም 4 ሺህ 892 ኪሎ ሜትር ያረጁ የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመሮች መጠገናቸውን ገልጸዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው አክለውም ከ67 በመቶ በላይ አገልግሎቱ የሚጠቀምባቸው ትራንስፎርመሮች በሀገር ውስጥ የመሚመረቱ መሆናቸውን ጨምረው አስታውቀዋል።
ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ለሚገጥሙ የስነምግባር ችግሮች ፈጣንና ተመጣጣኝ እርምጃዎች መውሰዱንና ይህም አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም ከአንድ ሚሊየን አንድ መቶ አስራ ሶስት ሺህ አንድ አዳዲስ ደንበኞችን ለማፍራት እንዲሁም 317 የገጠር መንደሮች አዲስ ኀይል እንዲያገኙ መታቀዱን አስታውቀዋል።
ከመሰረተ ልማት ማስፋፊያና ጥገና አንጻርም በአዲሱ በጀት ዓመት 12 ሺህ 549 ኪሎ ሜትር የኤሌክትሪክ መስመር እንደሚዘረጋም ገልጸዋል።
የኤሌክትሪክ መቆራረጥን መቀነስ የሚያስችሉ ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እና ጥገና ስራዎች በትኩረት ይከናወናሉ ነው ያሉት።
አሁን ላይ አገልግሎቱ የሚጠቀምባቸው ከ67 በመቶ በላይ ትራንስፎርመሮች በሀገር ውስጥ እንደሚመረቱም ኢንጂነር ጌቱ ገረመው በመግለጫቸው ተናግረዋል።
የኀይል መቆራረጥ ምጣኔን ለመቀነስ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመው ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ለሚገጥሙ የስነምግባር ችግሮች ፈጣንና ተመጣጣኝ እርምጃዎች መውሰዱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።