የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ አደጋዎች በሰውና በንብረት ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን ጉዳት ለመከላከል የቅድመ-ጥንቃቄ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ አደጋዎች በሰውና በንብረት ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን ጉዳት ለመከላከል የቅድመ-ጥንቃቄ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 1/2018 (ኢዜአ)፦የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ አደጋዎች በሰውና በንብረት ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን ጉዳት ለመከላከል የቅድመ-ጥንቃቄ ሥራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለሰልጣን ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን ከደንብ ማስከበር ባለስልጣን ጋር በመሆን በወቅታዊ አደጋ ስጋቶችና በቅድመ-ጥንቃቄዎች ዙሪያ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽነር ኮማንደር አሕመድ መሐመድ እንደገለጹት፤ የአደጋ ስጋት ደህንነት ደንብ ቁጥር 132/2014 እና የአደጋ መከላከል፣ ቁጥጥር፣ ፍተሻና ብቃት ማረጋገጥ መመሪያ ቁጥር 163/2017 የህዝብን ህይወትና ንብረት ከአደጋ የመጠበቅ ያለሙ ናቸው፡፡
እነዚህ ህጎች የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ አደጋዎችን አስቀድሞ ለመከላከልና ጉዳቶችን ለመቀነስ የሚደረጉ ጥረቶችን የሚያጠናክሩ ናቸው ብለዋል።
በዚሁ መሠረት ከዛሬ ጀምሮ በተቋማት ደረጃ ለህብረተሰቡ የቴክኒክ ድጋፍና የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት አደጋን በጋራ የመከላከል ስራ በስፋት እንደሚከናወኑ ጠቅሰዋል፡፡
እንዲሁም የአደጋ መከላከልና ቁጥጥር ህጉን ለማስከበር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ጋር በመተባበር የህግ ማስከበር ስራዎች እንደሚሰሩም ጠቁመዋል፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን በመግለጫው እንደተናገሩት፤ አዲስ አበባ ዘመናዊ ህንጻዎች፣ ኢንዱስትሪዎች፣ የጤና ተቋማትና የዲፕሎማቲክ መኖሪያዎች የሚገኙባት ከተማ በመሆኗ ከእድገቷ ጋር ተያይዞ የሚመጡ አደጋዎችን ለመከላከል ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡
ይህንንም ለማስፈጸም የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን ያወጣቸውን የአደጋ ስጋት ደህንነት ደንብ ቁጥር 132/2014 እና መመሪያ ቁጥር 163/2017 በተግባር ለመተርጎም በጋራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ህጉ አደጋዎችን አስቀድሞ በመከላከል የሰዎችን ህይወትና ንብረት የመጠበቅ አላማ እንዳለውም አብራርተዋል።
በደንቡ መሰረት የሚከተሉት ድርጊቶች የተከለከሉ መሆናቸውን ጠቅሰው በአደጋ መከላከል ስራ ላይ በሚሰማሩ አካላት ላይ ጣልቃ መግባት፣በሲኒማ፣ ቲያትር፣ ስቴዲየምና ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ከተፈቀደው በላይ ሰዎችን ማስተናገድ ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ሰዎች ባሉበት ህንጻዎች ውስጥ የአደጋ ማምለጫ በሮችን መቆለፍ ወይም መዝጋት እንዲሁም ለአደጋ መቆጣጠርና ለድንገተኛ ህክምና የተመደቡ ተሽከርካሪዎችን ለሌላ አላማ ማዋል የተከለከሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ደንቡን ለማስፈጸም ከዛሬ ጀምሮ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እንደሚሰጥ የተገለፀ ሲሆን፣ መመሪያውን ተላልፈው በሚገኙ ተቋማትና ድርጅቶች ላይ ባለስልጣኑ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።