ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ፤ አዲሲቷ የዘመን ተሻጋሪ ዲጂታል ክህሎት የተስፋ አድማስ!!

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በወፍ በረር

“ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የታለመለትን ግብ አሳክቶ ተጠናቋል። በዛሬው ዕለትም ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን በይፋ አስጀምረናል። ተደራሽነትን ማስፋት፣ ለዜጎች እኩል ዕድል መፍጠር፣ እንዲሁም በዜጎችና ተቋማት መካከል መተማመንን ማጎልበት ደግሞ የስትራቴጂው ቁልፍ መሠረታዊ ትልሞች ናቸው። እነዚህ ትልሞች እንዲሳኩም በተለይ የሕዝብ ዲጂታል መሠረተ ልማትን ማስፋት ላይ ትልቅ ሥራ የሚከናወን ሲሆን፣ ይህም ዲጂታል ቴክኖሎጂ ሰው ተኮር ሆኖ የዜጎችን ኑሮ እንዲያሻሽል ትልቅ አቅም ይፈጥራል። በአጠቃላይ በዲጂታል ኢትዮጵያ የሚከናወኑ ሥራዎች የመደመር መንግሥት በቀለለ ቢሮክራሲ ታላላቅ ስትራቴጂዎችን እውን ለማድረግ ከያዘው ግብ ጋር የተሳሰሩ ናቸው።”

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

የኢትዮጵያ ዲጅታላይዜሽን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሚመራ ብሔራዊ የልማትና ዕድገት ፕሮግራም ነው። እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2020 በዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ማዕቀፍ ይፋ የተደረገው ብሔራዊ አጀንዳ በዲጅታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂም ቁልፍ ጉዳይ ሆኖ ተይዟል።

ግቡም ሁሉንም ተቋማት በኢንፎርሜሽንና ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ በማስተሳሰር በኢትዮጵያ ፈጣን የዲጅታል ኢኮኖሚ ሽግግር መፍጠር ነው።

ዘመናዊ የሕዝብ አገልግሎት መስጠት፣ የኢንተርኔትና የዲጅታል ትስስርን ማስፋፋት፣ የዲጅታል ፋይናንስ አገልግሎትን ማላቅ፣ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ የጤና አጠባበቅና የትምህርት ሥርዓትን ማሻሻል፣ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የዲጅታል ኢኮኖሚ መገንባት፣ በኢንፎርሜሽንና ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ እንዲሁም በኢኖቬሽን የሥራ ዕድል መፍጠር እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማትን መደገፍ የዲጅታላይዜሽን መሠረቶች ናቸው።

የዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ

የዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ የዲጅታል ኢኮኖሚ መሠረት ጥሏል። በመንግሥት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥን በዲጅታል ቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት አስችሏል፤ ተጠያቂነት የሰፈነበት የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋትም ብልሹ አሠራርን ለመከላከል የሚያስችል መሠረት ጥሏል።

የዲጅታል ማንነትን በማስፋፋት ዜጎች አገልግሎቶችን በኤሌክትሮኒክ ሥርዓት ማግኘት እንዲችሉ ያስቻለ ሲሆን፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን፣ ቅንጅትንና ተደራሽነትንም አሳድጓል። ቀደም ሲል ዜጎች ዲጅታል ማንነት መጠቀም በማይችሉበት ወቅት በርካታ የወረቀት ሰነዶችን ከማቅረብ ጀምሮ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትን በመዳረስ ረጅም ጊዜና ጉልበት ያጠፉ ነበር።

አሁን ግን ሁኔታው ተለውጧል። በወረቀት አልባ ሥርዓት ፈጣንና ፍትሐዊ የመንግሥት አገልግሎት ማግኘት የሚቻልበት የዲጅታል ምህዳር ተፈጥሯል፤ የዜጎች እንግልት ቀንሷል፤ ወረፋና ጥበቃም ተረት ሆኗል።

የዲጅታል ክፍያ ሥርዓትም በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንደዕለት ተዕለት አጠቃቀም ቀላልና የተለመደ እየሆነ መጥቷል። የቴሌኮም መሠረተ ልማትን የማስፋፋት ሥራም ተጠናክሯል፤ የዲጅታል ክህሎት በተለይም በወጣቶች ዘንድ አዲስ የእውቀትና የተወዳዳሪነት መሣሪያ ሆኗል። ለዲጅታል መሠረተ ልማት መስፋፋት ቁልፍ የሆኑ ሕጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፎችም ተፈጥረዋል።

የዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ለኢትዮጵያ የዲጅታል ኢኮኖሚ ሽግግር መሠረት ጥሏል፤ የኢትዮጵያን መጪ ጊዜ በተስፋ መመልከት የሚያስችል አጉሊ መነጽር አቅርቧል። በዲጅታል ክፍያዎች የታገዘ የጥሬ ገንዘብ አልባ ግብይትም የሀገሪቱን አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እያዘመነ ይገኛል።

ጥሬ ገንዘብ በእጅ የመያዝ ልማድ መቀነሱ የገንዘብ ማተሚያና ማጓጓዣ ወጪን ቀንሷል፤ የገንዘብ ዝውውርን ግልጽና ፈጣን በማድረግም ሕገወጥ አሠራሮችንና ሙስናን ለመከላከል አስችሏል። ጠንካራ የሳይበር ደህንነት ጥበቃ ከተደረገለት የፋይናንስ ሥርዓት ጋር ሲቀናጅም፣ ሕዝቡ በዲጅታል ክፍያዎች ላይ ያለው መተማመን እንዲጎለብት ያደርጋል፤ የሀገሪቱንም የዲጅታል ሽግግር ጉዞ ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል። ይህም ለዲጅታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ መሠረት ጥሏል።

የዲጅታል ኢትዮጵያ 2030፤ የሽግግሩ ቀጣይ ምዕራፍ

የዲጅታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነትን በማጠናከር፣ የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት አገልግሎቶችን ፍጥነት፣ ተደራሽነትና ግልጽነት ለማሳደግ ያለመ ነው። ይህም የመንግሥትን ወጪ ለመቀነስና የአገልግሎት ብቃትን ለማሳደግ ዕድል ይፈጥራል።

የዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ስኬትም በኢኮኖሚ፣ በትምህርትና በአገልግሎት ዘርፎች አዎንታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል። የሀገሪቱ የዲጅታል ሽግግር በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድና በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ በተመሠረተው የዲጅታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ላይ የተቃኘ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በስትራቴጂ ማስጀመሪያው ወቅት፦ ስትራቴጂው በከተማም ሆነ በገጠር የዲጅታል ሥርዓትን በማስረጽ የዲጅታል ኢኮኖሚን እውን የምናደርግበት ነው ብለዋል።

ቁሳዊ ዕድገት የሚጀምረው የሰው ኃይል አቅምን በመገንባት እንደሆነ ጠቅሰው፣ ወጣቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ፣ የፈጠራ ባለቤቶችና ሥራ ፈጣሪዎች እንዲሆኑ በዲጅታል ክህሎት ማስታጠቅ እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተዋል።

የዲጅታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ ግቦች ኢትዮጵያ የብሮድባንድና ኢንተርኔት ተደራሽነትን በመላ ሀገሪቱ በመዘርጋት፣ የዜጎችና ተቋማትን የዲጅታል ክህሎት በማሳደግ፣ እንደ ግብርና፣ ቱሪዝም፣ አምራች ኢንዱስትሪዎችና ስታርትአፖችን በቴክኖሎጂ በማዘመን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትና ንግድን መሳብ፣ እንዲሁም አካታች የዲጅታል ኢኮኖሚ መገንባት ናቸው።

የዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የመንግሥት የዲጅታል አገልግሎት ማስፋፊያ፣ የቴሌኮም ሪፎርም፣ ዲጅታል ክፍያ፣ ብሔራዊ የዲጅታል መታወቂያ/ፋይዳ፣ እንዲሁም በሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ ዲጅታል የሕዝብ መሠረተ ልማት፣ የሳይበር ደህንነትና ብሔራዊ የዲጅታል አካታችነትን መርህ ያደረገውን የዲጅታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ አዋልዷል።

የዲጅታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የዲጅታል ሽግግር ስትራቴጂ ነው። ከዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ስኬት የተቀዳ ታላቅ የመሆን ህልም ሥጋ ለብሶ የታየበት ግልጽ ፍኖተ ካርታም ነው። የዲጅታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም፣ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2030 ቀልጣፋ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ፣ የአስተዳደር ሥርዓትን በማጠናከር አገልግሎትን ማሻሻል፣ በዲጅታል ቴክኖሎጂ የበቃ ማኅበረሰብ በመፍጠር ሀገርን ማበልጸግ፣ ለነገ ዛሬ የሚኖር አደራና ዛሬ የነገ ስንቅ ሆኖ በግልጽ ሰፍሯል።

የኢትዮጵያ የዲጅታል ሽግግር ግብ አንድ ነው፤ አካታችና ዘላቂ ዲጅታል ኢኮኖሚ መገንባት፣ በዋጋ ተመጣጣኝና ተደራሽ የኢንተርኔትና የኮሙኒኬሽን አገልግሎትን ማስፋት፣ በዲጅታል ኢኮኖሚ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የመረጃ አስተዳደርና የሳይበር ደህንነት ጥበቃን ሕልው ማድረግ፣ የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነትን መጨመር፣ ዲጅታል ክህሎትና ኢኖቬሽንን ማሳለጥ ነው።


 

ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ /ፋይዳ/፤ የዲጅታል ሽግግር መልህቅ

''በቅርብ ዓመታት ውስጥ፣ ዲጅታል ማንነት ተስፋ ሰጪ ከሆነው ፈጠራ ወደ ዲጅታል ሽግግር መሠረታዊ ምሰሶ ተሻሽሏል። ከአሁን በኋላ አማራጭ ሳይሆን፣ ሰዎችን ከአገልግሎቶች፣ ከማኅበረሰቦች፣ ከተቋማት እና ከመንግሥታት ጋር የሚያገናኝ አስፈላጊ መሠረተ ልማት ነው። ፋይዳ ካርድ ብቻ አይደለም። የግለሰቦችን የግል መረጃ ምሥጢራዊነት በመጠበቅና አስፈላጊ የሆነውን መረጃ ብቻ በማጋራት ማንነትን የሚያረጋግጥ ልዩ መለያ ቁጥር ነው።”     

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ /ፋይዳ/፤ የዲጅታል ሽግግር መልህቅ

የዲጅታል ብሔራዊ መታወቂያ /ፋይዳ/ (National Digital ID) በኢትዮጵያ ሥራ የጀመረው እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2023 ነበር። ምንም እንኳን የፕሮጀክቱ ዝግጅትና ሕጋዊ መሠረት ቀደም ብሎ የተጀመረ ቢሆንም፣ በአዋጅ ቁጥር 1284/2015 በሕግ ተቋቁሟል። እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር ከ2019 እስከ 2020 ባለው ጊዜም ፋይዳ በዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ አካል ሆነ። ከዚያም ምዝገባው በመላ ኢትዮጵያ ተስፋፍቶ፣ ከመንግሥት አገልግሎቶች፣ ከባንኮች፣ ከዲጅታል ክፍያ ሥርዓት እና ከመሶብ የአንድ ማዕከል ዲጅታል አገልግሎት ጋር ተሳስሯል።

በኢትዮጵያ እያንዳንዱን ነዋሪ የአንድ ልዩ የዲጅታል መለያ ባለቤት ማድረግ የፕሮጀክቱ ዋነኛ ግብ ነው። ይህም የመንግሥትና የግል አገልግሎቶችን በቀላሉ ማግኘት የሚቻልበትን ሥርዓት ለመዘርጋት፣ የማንነት ማጭበርበርና ድርብ ምዝገባን ለማስቀረት እንዲሁም የኢትዮጵያን ዲጅታል ኢኮኖሚ ለመደገፍ ያስችላል።

ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የነዋሪዎችን የባዮሜትሪክና ዲሞግራፊክ መረጃ በመሰብሰብ፣ ''አንድ ሰው፣ አንድ ማንነት” በሚል መርህ እያንዳንዱን ሰው ልዩ በሆነ ሁኔታ መለየት የሚያስችል ሥርዓት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ስለፋይዳ አስፈላጊነት ሲናገሩ፣ “ፋይዳ በአማርኛ፣ በኦሮሚኛ፣ በትግርኛ፣ በሱማሊኛ፣ በአፋርኛ እንዲሁም በአረብኛ፣ በሂንዱኛና በተርኪሽ ቋንቋዎች ፋይዳ ነው። … ዲጅታል መታወቂያ /ፋይዳ/ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው፤ ከሕዳሴ የሚያንስ አይደለም። እንደ ሀገር ዲጅታል መታወቂያ ብንሠራ የኢትዮጵያ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርት በሰባት ፐርሰንት ይጨምራል። ፋይዳ የመተማመኛ ሥርዓት ነው…” በማለት የፋይዳን መልከ ብዙ ፋይዳ ገልጸዋል። ፋይዳ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና የዲጅታል ኢኮኖሚ ሽግግሩን ለማሳለጥ ቁልፍ መሣሪያ መሆኑንም አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ከ150 በላይ ተቋማት ጋር ተሳስሯል። ከ48 ሚሊዮን በላይ ዜጎችም ተመዝግበዋል። እስከ 2020 ዓ.ም ድረስ የተመዝጋቢዎችን ቁጥር ወደ 115 ሚሊዮን ለማድረስ ጉዞው ቀጥሏል። በዚህም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ወደ መደበኛ የፋይናንስ ሥርዓት ለማስገባት እያገዘ ይገኛል።

መንገዶች ሁሉ ኢትዮጵያን ወደ ዲጅታል ሽግግር በሚወስዱበት ሀዲድ፣ ፋይዳ መሪ ተዋናይ ሆኖ ይቀጥላል። ዜጎች ፈጣንና ቀልጣፋ የመንግሥት አገልግሎት እንዲያገኙ፣ የባንክና የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲጠቀሙ የሚያስችል የቴክኖሎጂ ምህዳር ይፈጥራል።

መንግሥትም ማጭበርበርን ለመከላከል፣ በተቋማት መካከል ግልጽና የተቀናጀ ትብብርን ለመዘርጋት እና የተሻለ የሕዝብ አገልግሎት የሚሰጥበትን ዕድል እውን ለማድረግ ፋይዳን ይጠቀማል። የቢዝነስ አንቀሳቃሾችም ዲጅታል ግብይትን፣ ፋይናንስንና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሥራቸውን የበለጠ ቀልጣፋና ተደራሽ ማድረግ ይችላሉ። በአጭሩ፣ ፋይዳ ''ሁሉ በእጄ፣ ሁሉ በደጄ” የሚለውን የዲጅታል ኢኮኖሚ ራዕይ እውን ለማድረግ የሚያግዝ ቁልፍ መሠረተ ልማት ነው።


 

መሶብ፤ የአንድ ማዕከል ዲጅታል አገልግሎት የጊዜና የቦታ ልጓም

''ሀገራዊ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሠረታዊ የሆነ የባህል ለውጥ ያስፈልጋል። ካቀድናቸው አምስት የልማት ምሰሶዎች መካከል ቴክኖሎጂን ለአገልግሎት ዘርፉ እንደ ዋነኛ መሣሪያ በመጠቀም፣ የአገልግሎት ቅልጥፍናንና ተደራሽነትን ለማሻሻል በቁርጠኝነት እየሠራን እንገኛለን። መሶብ የአንድ ማዕከል የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን ተግባራዊ ማድረግ የጀመርነው በቅርብ ጊዜ ቢሆንም፣ በመሶብ አገልግሎቶች የታየው ከፍተኛ የደንበኞች እርካታ የዚህን የሥራ ሞዴል ውጤታማነት በግልጽ አረጋግጧል። ይህም አሠራሩን ይበልጥ ማስፋፋት አስፈላጊ መሆኑን ያመላክታል።”ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

                                         

መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጅታል አገልግሎት፤ የጊዜና የቦታ ልጓም

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት 12 የፌዴራል ተቋማት 40 የተለያዩ አገልግሎቶችን በአንድ ጣሪያ ሥር እንዲሰጡ በማድረግ ሚያዚያ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ተመርቆ ሥራ ጀምሯል።

እነሆ ማዕከሉ የተቋማትንና የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ቁጥር እያሳደገ የኢትዮጵያን የዲጅታል ሽግግር ፍኖት እየቀረጸ ይገኛል። ዜጎችም በዲጅታል መሠረተ ልማት የተደገፈ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ተደራሽ አገልግሎት ማግኘት ጀምረዋል።

ከዚህ በፊት የዜጎችን ጊዜ የሚያባክኑ ረጅም ወረፋዎች፣ የተለያዩ ቢሮዎችን ደጋግሞ መጎብኘት፣ “ሰነድ ይጎድላል፣ ኮፒ አድርገህ አምጣ” የሚሉ የወረቀት ሥራዎች በአዲሱ የአገልግሎት ሥርዓት እየተቀየሩ ነው።

አዲስ የአገልግሎት አድማስ የሆነው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከ220 በላይ የመንግሥት አገልግሎቶችን በአንድ ሕንፃ ሥር በማቅረብ የዜጎችን የጊዜና የቦታ ጫና ቀንሷል።

ከቀበሌ መታወቂያ ማውጣት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የንግድና የጉምሩክ አገልግሎቶች ድረስ በቀላሉ ማግኘት የሚቻልበት ምቹ ምህዳር ተፈጥሯል። ፈጣንነት፣ ቅልጥፍና፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዋና መርሆዎች ሆነዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተንቀሳቃሽ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ባስጀመሩበት ወቅት፤ ዜጎቻችን ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙና ትርጉም ያለው የጊዜ ቁጠባ እንዲያገኙ ለማስቻል፣ እነዚህን የተቀናጁ አገልግሎቶች ይበልጥ ተደራሽ የማድረግ ሥራችንን እንቀጥላለን ብለዋል።

 የዲጅታል አገልግሎት የዜጎችን ጊዜና ጉልበት የሚቆጥብ አዲስ የአስተዳደር ባህል መሆኑን ገልጸዋል። በአጠቃላይ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የወረቀት እና የወረፋ ዘመንን በመቀየር ዜጋን ማዕከል ያደረገ፣ ቀልጣፋና ዲጅታል የሆነ የአገልግሎት ሥርዓት እየገነባ ያለ የለውጥ ምሳሌ ሆኗል።


 

 

የ5-ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮች ኢንሼቲቭ፤ የዲጅታል ክህሎት ማበልጸጊያ መድረክ

በዲጅታል ዘመን የሰው ኃይል አቅም የሀገራት የዕድገት መሰረት እሆነ ነው። ኢትዮጵያም የወጣቶቿን የፈጠራና የቴክኖሎጂ አቅም ለማሳደግ ትልቅ የዲጅታል ክህሎት ማበልጸጊያ መርሃ ግብር ጀምራለች።

የ5-ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደርስ ኢንሼቲቭ የወጣቱን ትውልድ የፕሮግራሚንግ፣ የሶፍትዌር ልማት፣ የፈጠራ ሥራና የዲጅታል ቴክኖሎጂ አቅም ለማጎልበት የተቀረፀ ሀገራዊ አጀንዳ ነው። መርሃ ግብሩ ወጣቶችን የዲጅታል ኢኮኖሚ ተሳታፊዎች ብቻ ሳይሆኑ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎችና የሀገር በቀል መፍትሔ አበልጻጊዎች ለማድረግ ያለመ ነው። 

''ይህም ኢትዮጵያ በዓለም የዲጅታል ውድድር ውስጥ የምትኖራትን ሚና ለማሳደግ፣ የቴክኖሎጂ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና በአፍሪካ የፈጠራ ማዕከል ለመሆን የሚያግዝ የወደፊት ራዕይ ነው። ኢትዮጵያ ወደፊት የሚያልሙ አሳቢ ወጣት ዜጎቿ ተስፋ አላት። የ‘አምስት ሚሊዮን ኮደርስ’ መርሃ ግብር ታላቅ እድል ነው። አምስት ሚሊዮኖቹ ኮደሮች ሀገር በቀል መፍትሔዎችን የሚሰጡ ብቻ ሳይሆኑ፣ ለአህጉራችን የተስፋ ብርሃን የሚፈነጥቁ ናቸው።''ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

በአጠቃላይ 5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮች ኢንሼቲቭ የዲጅታል ክህሎትን ከመገንባት ባሻገር፣ የወጣቱን የፈጠራ ኃይል ወደ ሀገራዊ የዕድገት ሞተር ለመቀየር የተቀረፀ የዲጅታል ኢትዮጵያ 2030 ዋነኛ መሠረት ነው። 

5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደርስ ኢንሼቲቭ፤ የዲጅታል ክህሎት ማበልጸጊያና የወጣቱ የወደፊት አቅም 

በፍጥነት በሚለዋወጠው የዲጅታል ዓለም ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት መያዝ አማራጭ ሳይሆን የዘመኑ ግዴታ ሆኗል። ዛሬ ላይ በመትጋት ነገን ማልማት የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ሲሆን፣ የሀገር ዕድገትም የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ላይ ይመሰረታል።

መንግሥት የበለጸገችና በቴክኖሎጂ የተደገፈች ኢትዮጵያን ለመገንባት ከለያቸው አምስት ቁልፍ የትኩረት መስኮች መካከል አይ.ሲ.ቲ (ICT) አንዱ ነው። በዚህ ራዕይ መሠረት የዲጅታል ኢኮኖሚ ግንባታን ለማሳለጥ ሦስት ቁልፍ የዲጅታል ሽግግር ማስፈጸሚያዎች ተግባራዊ ሆነዋል። እነሱም መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጅታል አገልግሎት፣ ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ (ፋይዳ) እና 5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮች ኢንሼቲቭ ናቸው።

የወጣቱን የዲጅታል አቅም የሚገነባ ታላቅ ኢንሼቲቭ

5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮች ኢንሼቲቭ በኢትዮጵያና በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ትብብር ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ በሦስት ዓመታት ውስጥ 5 ሚሊዮን ወጣቶችን በዲጅታል ክህሎት ለማሰልጠን የተቀረጸ ፕሮግራም ነው። ፕሮግራሚንግ (Programming)፣ የመረጃ ትንተና (Data Analysis)፣ የአንድሮይድ ልማት (Android Development) እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት መሠረቶች (Artificial Intelligence Fundamentals) የሥልጠናው ዋና የክህሎት ዘርፎች ናቸው።

ኢንሼቲቩ የተያዘለትን ግብ በፍጥነት እያሳካ ይገኛል። ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ከ5 ሚሊዮን በላይ ሰልጣኞች ተመዝግበዋል፤ ቁጥሩን እስከ ነሐሴ 2018 ዓ.ም 7 ሚሊዮን ለማድረስ ዕቅድ ተይዟል።

ይህም የወጣቶችን ለሥራ ዓለም ተፈላጊነት ከማሳደግ ባሻገር፣ የሀገሪቱን የዲጅታል የሰው ኃይል ልማት ያጠናክራል። በመንግሥት ተቋማት የሶፍትዌር ልማትና የዲጅታል ሽግግር ሥራዎችን የሚያሳልጡ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችንም ያፈራል።

በኢንሼቲቩ አማካኝነት 1 ሚሊዮን የዲጅታል የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ከዲጅታል ምርቶች ወጪ ንግድ 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት የተቀመጠው ዕቅድ የፕሮግራሙን ሀገራዊ ፋይዳ ያመላክታል።

የወጣቶች የፈጠራ ኃይል የኢትዮጵያ የዲጅታል ተስፋ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በየትኛውም የትምህርትና የዕውቀት ደረጃ ላይ ያሉ ወጣቶች የአምስት ሚሊዮን ኮደሮች ፕሮጀክትን በመጠቀም ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከላት፣ አሰልጣኞችና ዩኒቨርሲቲዎችም የፕሮግራሙን ስኬት ለማስፋት የሚያደርጉት አስተዋፅኦ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የዲጅታል ሽግግር ሦስቱ ምሰሶዎች

በጥቅሉ 5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮች ኢንሼቲቭ፣ ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ (ፋይዳ) እና መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የኢትዮጵያን የዲጅታል ኢኮኖሚ ግንባታ የሚያስፈጽሙ ተያያዥ ምሰሶዎች ናቸው።

ኮደርስ የዲጅታል ኢኮኖሚውን የሚገነባና የሚያስፋፋ የሰው ኃይል ያበረክታሉ፤ ፋይዳ ደግሞ የደህንነቱ የተጠበቀ የዲጅታል ማንነት ሥርዓት ይፈጥራል፤ መሶብም በአንድ ጣሪያ ሥር ፈጣንና ግልጽ የህዝብ አገልግሎት ያሳልጣል።

ከዲጅታል ኢትዮጵያ 2030 ራዕይ ጋር ተጣምረው እነዚህ ሦስት የለውጥ ምሰሶዎች ኢትዮጵያን ወደ አካታች፣ ዘላቂና ተወዳዳሪ የዲጅታል ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው።


 

ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የኢትዮጵያ ተሻጋሪ ህልሞች መመልከቻ

በኢትዮጵያ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence) እ.ኤ.አ. በ2020 የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በመመስረት ተቋማዊ መሠረት የያዘ የልማት አቅጣጫ ሆኗል። የሰው ሰራሽ አስተውሎት ፖሊሲና ሕጋዊ ማዕቀፎች በመዘርጋታቸው ዘርፉ በተደራጀ አሠራር እንዲመራ ተደርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በጎበኙበት ወቅት፣ ሰው የጠራ ራዕይ ካለው፣ በከፍተኛ ዲሲፕሊን የሚሠራ ከሆነ ያሰበውን ማሳካት እንደሚችል፤ ኢትዮጵያ ብቃት ያላት ሀገር መሆኗን በመግለጽ የዘርፉን ሀገራዊ ጠቀሜታ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የሀገር ውስጥ የፈጠራ አቅምን በማበረታታት ዘርፈ ብዙ ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ መፍትሔዎች እንዲመነጩ እያደረገ ይገኛል። በግብርና፣ በጤና፣ በፋይናንስ፣ በደህንነትና በአገልግሎት ዘርፎች የሚያገለግሉ የሰው ሰራሽ አስተውሎት መፍትሔዎች በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች መፍጠር ጀምረዋል።

በአማርኛ፣ ኦሮምኛና ትግርኛ ቋንቋዎች የተዘጋጁ የጽሑፍና የድምፅ ማቀናበሪያ ቴክኖሎጂዎች (NLP)፣ በጤና ዘርፍ የጡት ካንሰር፣ የስኳር በሽታና የሳንባ በሽታዎችን በምስል ምርመራ ቀድመው ለመለየት የሚያግዙ የAI መፍትሔዎች፣ በግብርና ዘርፍ የቡናና የሰብል በሽታዎችን የሚለዩ መተግበሪያዎች እየተስፋፉ ነው።

በተጨማሪም ለከተማ ደህንነት፣ ለፖሊስ ሥራ፣ ለጉምሩክ ቁጥጥርና ለፋይናንስ ተቋማት የሚያገለግሉ ቻትቦቶችና ሌሎች የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች በመስኩ እየተተገበሩ ይገኛሉ። የታዳጊዎች የሰመር ካምፕ የAI ስልጠናዎችም የወደፊቱን የቴክኖሎጂ ባለሙያ ትውልድ ለማፍራት እያገዙ ናቸው።

የኢትዮጵያ የዲጅታል ሽግግርና የሰው ሰራሽ አስተውሎት ጉዞ በሀገር ድንበር የማይገደብ፣ የአፍሪካን ዲጂታል ሽግግር ታሳቢ ያደረገ አህጉራዊ ራዕይ ነው። ለዚህም ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኮንፈረንስን በማዘጋጀት አፍሪካ በዲጂታል ሽግግር፣ በፈጠራና በቴክኖሎጂ ትብብር እንድትጠናከር ያላትን ራዕይ አሳይታለች።

በአፍሪካ ቀዳሚ ከሚሆኑ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከላት አንዱ የሆነው የAI ዩኒቨርሲቲ ግንባታም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ለማሳካት፣ የአፍሪካን የቴክኖሎጂና የፈጠራ አቅም ለማሳደግ የተያዘ ተሻጋሪ ራዕይ ነው። በአጠቃላይ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ለኢትዮጵያ የወደፊት የዕውቀት ኢኮኖሚ፣ የፈጠራ አቅምና የዲጂታል ሉዓላዊነት መሠረት እየሆነ የሚሄድ ተሻጋሪ መሣሪያ ነው።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፤ የዲጅታል ሉዓላዊነት እና ቁልፍ መሠረተ ልማቶች ዘብ

የዓለም የዲጅታላይዜሽን ሽግግር በብርሃን ፍጥነት እየተስፋፋ ባለበት ዘመን፣ ቴክኖሎጂን መጠቀም ብቻ ሳይሆን የዲጅታል መሠረተ ልማቶችን ከሳይበር ስጋቶች መጠበቅ የሀገራት ቁልፍ ተግባር ሆኗል። በዚህ የቴክኖሎጂ ውድድር ዓለም የመረጃ ደህንነት ከቴክኒክ ጉዳይ ባለፈ የሀገር ሉዓላዊነትና ህልውና ጉዳይ እየሆነ መጥቷል።

ኢትዮጵያም የዘግይቶ መግባት ጥቅም (Latecomer Advantage) በመጠቀም የዲጅታል ሽግግሯን በዘመናዊ መሠረተ ልማቶች ላይ ለመገንባት እየሠራች ትገኛለች። ይህንን የዲጅታል ጉዞ አስተማማኝ ለማድረግና የሀገሪቱን የመረጃ ሀብት ለመጠበቅ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (INSA) ወሳኝ ሚና እየተወጣ ነው።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የኢትዮጵያን የኢንፎርሜሽን ሥርዓቶችና ቁልፍ የመረጃ መሠረተ ልማቶች ከሳይበር ጥቃት የመጠበቅ፣ የመረጃ ደህንነትን የማረጋገጥና ብሔራዊ ጥቅሞችን የማስከበር ተልዕኮ ተሰጥቶታል።

የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ፣ የደህንነት ኦፕሬሽን ማዕከላት (Security Operation Centers) እና የዲጅታል ፎረንሲክ ላቦራቶሪዎች ግንባታ ለዘርፉ የተሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

እነዚህ ዘመናዊ የዲጅታል ደህንነት መሠረተ ልማቶች እንደ ባንክ፣ ቴሌኮም፣ የኃይል አቅርቦትና ሌሎች ቁልፍ ሀገራዊ ተቋማትን ከተወሳሰቡ የሳይበር ጥቃቶች አስቀድሞ ለመከላከል፣ አደጋ ቢከሰትም ፈጣን ሕጋዊና ቴክኒካዊ ምላሽ ለመስጠት ያስችላሉ።

የመረጃ ደህንነት፤ የዲጅታል ኢኮኖሚ መሠረት

በዛሬው ዓለም መረጃ (Data) እንደ አንዱ ዋና ሀብት በመቆጠሩ፣ የዜጎችን ግላዊ መረጃ፣ የፋይናንስ ግብይቶችንና የመንግሥት ሚስጥራዊ መረጃዎችን በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅ የዲጅታል ሉዓላዊነት ዋና መሠረት ሆኗል።

ጠንካራ የሳይበር ደህንነት ሥርዓት መኖሩ ዜጎች በዲጅታል አገልግሎቶች ላይ እምነት እንዲያሳድሩ፣ የግልና የውጭ ባለሀብቶችም በኢትዮጵያ የዲጅታል ኢኮኖሚ ላይ የተሻለ እምነት እንዲኖራቸው ያደርጋል።

በዚህም የሳይበር ደህንነት የዲጅታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ስኬትን የሚደግፍ ዋና የጥበቃ መሠረት ሆኖ ይቀጥላል።

ማጠቃለያ፡ ዲጂታል ኢትዮጵያ፤ የወደፊት ተወዳዳሪነት መሠረት

የኢትዮጵያ የዲጂታል ሽግግር ጉዞ ከፖሊሲ ቀረጻ እስከ ተግባራዊ የዲጂታል መሠረተ ልማት ዝርጋታ በፍጥነት እየተሻገረ ይገኛል። ይህ ሀገራዊ ንቅናቄ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የሚመራ ሲሆን፣ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ /ፋይዳ፣ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት፣ አምስት ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮች ኢኒሼቲቭ፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ልማትና የሳይበር ደህንነት ሥርዓት ዋና ዋና የሽግግሩ ምሰሶዎች ሆነዋል።

ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ /ፋይዳ የዜጎችን ዲጂታል ማንነት በማረጋገጥ ለዲጂታል አገልግሎቶች መሠረት ሲሆን፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የሕዝብ አገልግሎትን በፍጥነት፣ በቅልጥፍናና በግልጽነት ለማቅረብ አዲስ የአሠራር ባህል እየገነባ ነው። አምስት ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮች ኢኒሼቲቭ ደግሞ ለዲጂታል ኢኮኖሚው የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል በማፍራት የቴክኖሎጂ ፈጠራና የዲጂታል ሥራ ዕድል እድገትን ያፋጥናል።

የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ዩኒቨርሲቲና የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ልማት ተቋማት የወደፊቱን የእውቀትና የፈጠራ አቅም ለመገንባት ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል። በተመሳሳይም የሳይበር ደህንነት ሥርዓት የዲጂታል ኢኮኖሚውን ከስጋቶች የሚጠብቅ፣ የመረጃ ደህንነትንና የሀገር ዲጂታል ሉዓላዊነትን የሚያስከብር ጠንካራ ጋሻ ሆኖ ይቀጥላል።

በቴክኖሎጂ፣ በኢኖቬሽንና በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፎች ኢትዮጵያ እየወሰደች ያለችው መዋቅራዊ እርምጃ የአገር ውስጥ አገልግሎቶችን ከማዘመንና የዜጎችን ኑሮ ከማቅለል ባለፈ፣ ሀገሪቱን በቀጣናውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ፣ አካታችና በእውቀት ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ባለቤት ለማድረግ የሚያግዝ ነው።

ኢትዮጵያ አዲስ የተስፋ አድማስ፡- '’ኢትዮጵያዊነት ያስተማረን ትልቁ እውነት፤ በጊዜያዊ ፈተናዎች ተሸንፎ መውደቅ ሳይሆን፣ ችግሮችን ወደ ዕድል፣ ፈተናዎችንም ወደ ስኬት መለወጥና ድልን መቀዳጀት ነው።ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ያስመዘገባቸው ውጤቶች ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ቀጣይ የልህቀት ጉዞ ጠንካራ መነሻና መሠረት ይሆናሉ። በመሆኑም ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታዋን ለማፋጠን በኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተጀመሩ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በተቀናጀ መንገድ በጋራ ገቢራዊ ማድረግ ይጠበቅባታል። ዲጂታል ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ራዕይ ብቻ ሳይሆን፤ የእውቀት፣ የፈጠራና የተወዳዳሪነት ሀገራዊ መሠረት ነው።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም