ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ተስፋ ያበሰረና ለአፍሪካውያንም አርዓያ የሚሆን ስኬታማ ምርጫ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ተስፋ ያበሰረና ለአፍሪካውያንም አርዓያ የሚሆን ስኬታማ ምርጫ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 1/2018 (ኢዜአ)፦ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ተስፋ ያበሰረና ለአፍሪካውያንም አርዓያ የሚሆን ስኬታማ ምርጫ ነው ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ብልፅግና ፓርቲ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ያገኘውን የህዝብ ውክልና ወደ ተጨባጭ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ስኬቶች ለመቀየር በሙሉ አቅሙ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በማስመልከት ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ማብራሪያ ሰጥቷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የብልፅግና ፓርቲ የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) እንደገለፁት፣ ፓርቲው በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ ከፍተኛ ቁርጠኝነት በመሰነቅ እና ሁለት ዋና ዋና ግቦችን ይዞ ወደ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ገብቷል።
የመጀመሪያውን ግብ አስመልከተው ሲያስረዱ፣ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊ እና ነፃ በማድረግ ኢትዮጵያውያን ሀሳባቸውን እና ድምፃቸውን በነፃነት የሚገልጹበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደነበር ገልፀዋል።
በዚህም በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ግንባታ ላይ የህዝቡ ተስፋ እንዲለመልም እና ዲሞክራሲ መሰረት እንዲይዝ ፓርቲው የሚጠበቅበትን ሀላፊነት በቁርጠኝነት መወጣቱን ገልፀዋል።
ብልፅግና ፓርቲ አብላጫ ድምፅ አግኝቶ መንግስት የመመስረት አላማ ብቻ ሳይሆን የነበረው፣ ምርጫው ነፃ እና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የመሪነት ሚና መጫወት እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
ሂደቱም የዴሞክራሲ ተስፋን የሰጠ እና ለአፍሪካውያንም ተሞክሮ ሊሆን የሚችል ውጤታማ ምርጫ እንደነበር ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ አስገንዝበዋል።
ፓርቲው በበርካታ እጩዎች ተወዳድሮ ከኢትዮጵያ ህዝብ አብላጫ ድምፅ በማግኘት መንግስት ለመመስረት የሚያስችል አዲስ ህዝባዊ ውክልና ማግኘቱን አብራርተዋል።
በሚቀጥሉት አምስት አመታትም የፓርቲውን ማኒፌስቶ ወደ እቅድ እና ስትራቴጂ በመቀየር ለህዝብ የገባውን ቃል ወደ ተግባር እንደሚቀይር ገልፀዋል።
በዚህም ትኩረቱ የኢትዮጵያን ዲሞክራሲ ማሻገር ብቻ ሳይሆን ህዝቡን ከድህነት ማውጣት፣ የምግብ ሉአላዊነትንና ዋስትናን ማረጋገጥ እንዲሁም ኢትዮጵያን በአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ማድረግ ላይ እንደሆነ አስታውቀዋል።
በብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ስሁል በበኩላቸው፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድንቅ በሆነ መንገድ መከናወኑን ገልፀዋል።
የዛሬው መድረክ በዋናነት ከምርጫው መጠናቀቅ በኋላ የተከናወኑ የድህረ ምርጫ የሚዲያ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ስራዎችን ለማስረገጥ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ እና አብረዉ ሲሰሩ የቆዩ የበርካታ ሀገራት አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች በመድረኩ መገኘታቸውን ገልፀው፤ የዝግጅቱ ዓላማ በአጠቃላይ ሂደቱ ላይ የጋራ መግባባት እና መረዳትን ለመፍጠር ያለመ እና ውጤታማ የሆነ መድረክ እንደነበር ገልፀዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ501 ውስጥ 438ቱን መቀመጫዎች ማግኘቱን ጠቅሰው ከክልል ምክር ቤት 2ሺህ 700 መቀመጫዎች ውስጥም 2ሺህ 410 መቀመጫዎች ማግኘቱን ተጠቅሷል፡፡
በሌላ መልኩም 8 የተፎካካሪ ፓርቲዎች መቀመጫ ማግኘታቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም 49 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን እና 246 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችን ማግኘታቸውን በዚሁ ወቅት አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ የራሺያ አምባሳደር ኤቭጌኒ ቴሬክሂን በሰጡት አስተያየት፤ በስኬት የተካሄደውን ሰባተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለኢትዮጵውያን ትልቅ ድል ነው ብለዋል፡፡
በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የህዝቡን የሰላም፣ የብልፅግና እና የእድገት ፍላጎት ያረጋገጠ ትልቅ ክስተት በመሆኑ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ስኬትን እመኛለሁ ብለዋል።
በኢትዮጵያ የኡጋንዳ አምባሳደር ሬቤካ አሙጌ ኦቴንጎ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት በመጠናቀቁ ለኢትዮጵያ ህዝቡና ለብልፅግና ፓርቲ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
ከማብራሪያው መጠናቀቅ በኋላ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉት አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ የተቋማት ተወካዮች እና የዓለማቀፍ ማህበረሰብ አባላት የብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት ቋሚ ኤግዚቢሽን ጎብኝተዋል፡፡