የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ የዳኞችን ሹመት በማፅደቅ ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ የዳኞችን ሹመት በማፅደቅ ተጠናቀቀ
ወልቂጤ፣ ነሐሴ 1/2018 (ኢዜአ)፦ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን፣ 6ኛ መደበኛ ጉባኤውን የክልሉን ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሪፖርት በማድመጥ እና የዳኞች ሹመትን በማፅደቅ ተጠናቋል።
የክልሉ ዋና ኦዲተር ወይዘሮ ፈዲላ አደም በጉባዔው ላይ እንደገለጹት፥ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በተከናወነው የኦዲት ሥራ ሊባክን የነበረ የመንግሥት እና የሕዝብ ሀብት መከላከልና ተመላሽ ማድረግ ተችሏል።
የኦዲት ተደራሽነትና ሽፋኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ያመለከቱት ዋና ኦዲተሯ፣ በፋይናንስ ኦዲት፣ በገቢ ግብር፣ በታክስና በሊዝ አሰባሰብ እንዲሁም በዓይነትና በአካባቢ ኦዲት ላይ የተሻለ ቢሆንም አሁንም በዘርፉ የሚታየውን የአሰራር ክፍተቶች ለማረም መረባረብ እንደሚገባ አስረድተዋል።
የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ በበኩላቸው፤ በክልሉ የኦዲት ግኝቶች ውጤታማ በሆነ መልኩ ምላሽ እንዲያገኙ የክልሉ ምክር ቤት ተገቢውን ድጋፍና እገዛ ማድረጉን ገልጸዋል።
የመንግስት በጀት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል በቀጣይም የኦዲት ግኝቶች በሙሉ ተመላሽ እንዲሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብርና በሙሉ አቅማቸው እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ምክር ቤቱ የቀረቡ የዳኝነት ሹመቶችን ያጸደቀ ሲሆን፣ ዛሬ ከተሾሙት 65 ዳኞች መካከል ለክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስምንት፣ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት 13 እና ቀሪዎች 44 ለወረዳና ለከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤት መሆናቸው ተገልጿል።
በጉባኤው ማጠቃለያ ባለፉት አምስት ዓመታት ሲያገለግሉ ለነበሩ የምክር ቤት አባለት እውቅና ተሰጥቷል።