ቀጥታ፡

የኤርትራ ህዝብ በአንድ ጨቋኝ ስርዓት ታፍኖ መኖር ሊበቃ ይገባል- ብርጌድ ንሓመዱ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 1/2018 (ኢዜአ)፦ የኤርትራ ህዝብ በአንድ ጨቋኝ ስርዓት ታፍኖ መኖር ሊያበቃና የስርዓት ለውጥ ሊመጣ እንደሚገባ የግንባር ሕዝባዊ ማዕበል ብርጌድ ንሓመዱ አስታወቀ።

የቀጣናውን ሰላም አደጋ ላይ ለመጣል በጦርነት ፍላጎት የተጠመደው ፅምዶ ተብሎ የሚጠራው የሽብር ቡድን ሕዝባዊ ድጋፍና መሠረት እንደሌለውም ነው የገለጸው።

የግንባር ህዝባዊ ማዕበል ብርጌድ ንሐመዶ የድርጅቱን ሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴና ቀጣናዊ ትብብር በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።

የግንባር ህዝባዊ ማዕበል ብርጌድ ንሓመዱ የፖለቲካና ዲፕሎማሲ ኃላፊ በየነ ገብረእግዚአብሔር እንዳሉት፤ ብርጌድ ንሓመዱ በኤርትራ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ማህበራዊ መሰረት ያለው እንቅስቃሴ ነው።

ግንባሩ የኤርትራን ዲያስፖራ በማደራጀት፣ በኤርትራ ያለውን ህዝብ የለውጥ ፍላጎት በማጠናከር ስርዓቱን ለመለወጥ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ሻዕቢያ የቀጣናውን ሰላም አደጋ ላይ ለመጣል በጦርነት ፍላጎት የተጠመደው ፅምዶ ተብሎ የሚጠራ የሽብር ቡድን አቋቁሞ እየሰራ መሆኑን በማነሳት፤ ይህ የጦርነት አባዜ የተጠናወተው ስብስብ ሕዝባዊ ድጋፍና መሠረት እንደሌለው አመልክተዋል።

ፅምዶ ለኤርትራም ሆነ ለትግራይ ሕዝብ የማይጠቅም ቀጣናውን ለማተራመስ የተዘጋጀ ስብስብ መሆኑንም ተናግረዋል።

የግንባር ህዝባዊ ማዕበል ብርጌድ ንሓመዱ ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ዳዊት ይብራህ፤ ግንባሩ በኤርትራ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ህዝባዊ መሰረት ይዞ መመስረቱን ተናግረዋል።

የኤርትራ ህዝብ በአንድ ጨቋኝ ስርዓት ታፍኖ መኖር ሊያበቃ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ለዚህ ህዝባዊ ለውጥ ማምጣት ጀምረናል ብለዋል።

ኤርትራ ከኢትዮጵያ እና ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጋር መልካም ጉርብትና እንዲኖራት ለማድረግ ስርዓቱን መለወጥ እንደሚገባም ገልጸዋል።

የግንባር ህዝባዊ ማዕበል ብርጌድ ንሓመዱ የዲፕሎማሲ ቡድን አባል ዳዊት ተፈሪ እንደገለጹት፤ የኤርትራ ህዝብ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በልማት እንዲተሳሰር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም