ቀጥታ፡

ጡት ማጥባት ሕፃናት የተስተካከለ እድገት እንዲኖራቸው የሚያስችል ተፈጥሯዊና ውጤታማ መንገድ ነው

ወልድያ፤ነሃሴ1/ 2018 (ኢዜአ) ፡-እናቶች ተፈጥሯዊ ስጦታቸው የሆነውን ጡት አጥብተው ልጆቻቸውን በማሳደግ ለአገር አለኝታ የሆነ ትውልድ ማፍራት እንደሚጠበቅባቸው የሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ።

መምሪያው በዓለም ለ35ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ18ኛ ጊዜ የሚከበረውን የጡት ማጥባት ሳምንት አስመልክቶ ከሐምሌ 25 እስከ ነሐሴ 01 ቀን 2018 ዓ.ም የግንዛቤ መፍጠሪያ የውይይት መድረክ አካሂዷል።


 

የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ ብርሃን ኃይሉ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ጡት ማጥባት የህፃናትን ጤንነትና ደህንነት በማስጠበቅ የነገ አምራች ዜጋ እንዲሆኑ መሰረት የሚጥል ነው።

የህጻናትን የተስተካከለ እድገት ለማረጋገጥና ጤናማ ትውልድ ለማፍራት ከፅንስ ጀምሮ ህጻኑ ተወልዶ እስከ ሁለት ዓመት ያለው ጊዜ የአመጋገብ ሁኔታን ማወቅ ለእናቶች አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

አንድ ህጻን ከተወለደ ጀምሮ እስከ ስድስት ወር ድረስ ያለምንም ተጨማሪ ምግብ የእናትን ጡት ብቻ መመገብ ተገቢ መሆኑን ጠቁመው፤ እስከ ሁለት ዓመት ከተጨማሪ ምግብ ጋር ማጥባት ወሳኝ ነው ብለዋል።

የዘንድሮው በዓል ሲከበርም ጡት ማጥባት በህጻናት እድገትና በእናቶች ጤና ላይ የሚያስገኘውን ጥቅምና ፋይዳ ግንዛቤ ለመፍጠርና ለማበረታታት ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህም ጤናማ ትውልድ በመገንባት የማህበረሰብ ልማትንና የአገርን ዘላቂ እድገት ለማስቀጠል መሰረት በመሆኑ ሁሉም ህብረተሰብ ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን የሰቆጣ ቃል ኪዳን አስተባባሪ የሆኑት አቶ ግዛቸው ታረቀኝ በበኩላቸው፤ ለሕፃናት የመጀመሪያው የበሽታ መከላከያ መንገድ የእናት ጡትን በተገቢው መንገድ መስጠት ነው።


 

ለዚሁ ስኬትም ለእናቶች በቂ ምግብ፣ እረፍት እንዲያገኙና ልጆቻቸውን ጡት አጥብተው እንዲያሳድጉ የሚያደርግ ጊዜ መስጠት እንደሚገባ አስረድተዋል።

ቃል ኪዳኑም የሚያጠቡና ነፍሰ ጡር እናቶችን በማቀፍ በጓሯቸው አትክልትና ፍራፍሬ እንዲያለሙ፣ በፍየል እርባታና በንብ ማነብ በመሰማራት በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ እየደገፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የዞኑ ወጣት በጎ ፈቃደኞች ተወካይ ንግስት ይመር እንዳለችው፤ የውይይት መድረኩ በቀጣይ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር ያስችለናል ብላለች።


 

“ጡት ማጥባት፤ ለዘላቂ የሕይወት ጅማሮ!” በሚል መሪ ሐሳብ በተካሄደው ውይይት ላይ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና የአጋር ድርጅት ተወካዮች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም