በክልሉ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ፍትሃዊነትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ፍትሃዊነትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 1/2018 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል የጤና አገልግሎት ተደራሽነትንና ፍትሃዊነትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ አብዱከሪም መንግስቱ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የዕድሳት የማስፋፊያ ግንባታና ዲጂታላይዜሽን ሥራ ምረቃ እና ሥራ ማስጀመሪያ መርሃግብር ተከናውኗል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ አብዱከሪም መንግስቱ እንደገለጹት ለነገው ትውልድ ዘላቂና የማይበገር የጤና ስርዓት ላይ ለመገንባት እየተሰራ ነው።
ፈጠራንና የአመራር ቅንጅትን በማጠናከር ጤናማ፣ አምራች፣ የበለጸገና ደስተኛ ማህበረሰብ ዜጋን ለመፍጠር በትጋት እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።
በክልሉ ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ፍትሃዊነትን ለማስጠበቅ በተከናወኑ ስራዎች ተጨባጭ ለውጦች መገኘታቸውን ገልጸዋል።
እነዚህ ለውጦች የተገኙት መንግስት ቁርጠኛ እርምጃዎችን በመውሰዱና የለውጥ ሀሳቦችንና ተግባራትን ተግባራዊ በማድረጉ ነው ብለዋል።
በዚህም ዜጎች ተደራሽ፣ ጥራት ያለውና ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት በአቅራቢያቸውና እና በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት ማስቻሉን ተናግረዋል።
የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎትን ማጠናከር፣ የጤና ተቋማትን ማስፋፋት፣ የመድሃኒትና የህክምና መሳሪያ አቅርቦትን ማሻሻል ላይ የተገኙ ስኬቶችንም አንስተዋል።
በዚህም የጤና ተቋማት በህክምና መሳሪያዎች እጥረት ሳቢያ ቀደም ሲል የማይሰጡ አገልግሎቶችን መስጠት ችለዋል ብለዋል።
ክልላዊና ሀገራዊ ኤንሼቲቮችን በመተግበርና ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር ውጤቶችን ማሳደግ መቻሉንም ገልጸዋል።
የተገኙ ውጤቶችን በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል በሀሳብ ከፍታና አንድነት እንተጋለን ብለዋል።