የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ኑሮ በማሻሻል የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ኑሮ በማሻሻል የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 1/2018 (ኢዜአ)፦ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተደመረ አቅም በመንቀሳቀስ የዜጎችን ኑሮ በማሻሻል የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን በብልፅግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ ገለጹ፡፡
በሀረሪ ከልል በክረምት በጎ ፍቃድ እየተከናወኑ በሚገኙ ተግባራት ዙሪያ ውይይት ተደርጓል።
በዚህ ወቅትም በብልፅግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ እንደገለጹት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተደመረ አቅም ዜጎችን በማገዝና ሃብትን አቀናጅቶ በመምራት ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
በተለይም በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ አቅመ ደካሞችንና አረጋዊያንን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ስራዎች እውን ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።
በዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ተግባራት በተጠናከረ መልኩ እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
በመርሃ ግብሩም በ14 መስኮች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም በአሁኑ ወቅት የአረጋውያንና አቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤት እድሳትና መልሶ ግንባታ፣ የአካባቢ ንጽህና ጥበቃ፣ ችግኝ ተከላ፣ ደም ልገሳ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት የመስጠትና ሌሎች ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ማዕድ ማጋራት፣ አዳዲስና ነባር የመማሪያ ክፍል ግንባታ እና እድሳት፣ የትምህርት ቤቶች የተማሪ ወንበሮች ጥገና፣ ጽዳትና ውበት ስራዎችን ጨምሮ የማጣቀሻ መጽሀፍት የማሰባሰብ ስራ በበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ መደጋገፍ፣ የመተጋገዝና አብሮነትን ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ጠቁመው የዜጎችን እውቀት፣ ገንዘብ፣ ጉልበት እና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎችን በሚገባ መጠቀምና ከድህነት መላቀቅ እንደሚያስፈልግ ነው የጠቆሙት።
አመራሩም በመርሃግብሩ የታቀዱ እቅዶች ወደ ተግባር ለመቀየር በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንዳለበት አሳስበዋል።