የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የአርሶ አደሮችን ምርታማነት አሳድጓል - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የአርሶ አደሮችን ምርታማነት አሳድጓል
አለታ ወንዶ ፤ ነሃሴ 1/2018 (ኢዜአ)፦ያለፉት ዓመታት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ተግባራት ምርታማነታቸው እንዲጨምር ማድረጉን በደቡባዊ ሲዳማ ዞን የአለታ ወንዶ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡
በወረዳው የዊቾ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ታፈሰ ዩጤ፤ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በየዓመቱ በግል ማሳቸውና በአካባቢው የወል መሬቶች ላይ ተከላ ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በአካባቢያቸው ተራቁተው የነበሩ ቦታዎች ለምልመው ወደ አረንጓዴነት መቀየራቸውን ጠቁመዋል።
በመርሃ ግብሩ የተከሏቸው የአቮካዶ፣ የማንጎ፣ የሙዝና ሌሎች ፍራፍሬዎች አሁን ላይ ለምርት በመድረሳቸው ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደጋቸውን ገልጸዋል።
የጎዋዳሞ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ካሰች ዳንሳሞ በበኩላቸው፤ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተከሏቸውን የፍራፍሬና የጥላ ችግኞች በመንከባከብ ለፍሬ እንዲበቁ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ችግኞቹ አድገው ለቡና ማሳቸው ጥላ ከመሆናቸውም በላይ፣ ፍራፍሬዎቹ ከምግብ ፍጆታ ባለፈ የገቢ ምንጫቸውን ለማሳደግ እንዳስቻላቸው አስረድተዋል።
የተሻሻሉ የአቮካዶ ዝርያዎችን በስፋት በማልማት ምርቱን ለኢንዱስትሪና ለሌሎች ገበያዎች እያቀረበ ተጠቃሚ መሆኑን ያነሳው ደግሞ የዶቤ ሰዴቃ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ወጣት ቹቹ ቢረጋ ነው።
በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን የፍራፍሬ ችግኞች በመትከል ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል።
የደቡባዊ ሲዳማ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደበበ ሻላ፤ በዞኑ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የአካባቢ ሥነ-ምህዳር መጠበቁንና የአርሶ አደሩ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማደጉን ገልጸዋል።
በዚም ለደንና ለምግብ የሚሆኑ ችግኞች መተከላቸውን በማንሳት፤ የአፈር ለምነትን ለመጠበቅና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ማስቻሉን ጠቅሰዋል።
ለአብነትም በመርሃ ግብሩ ከተተከሉ ጥምር ጥቅም የሚሰጡ ችግኞች መካከል የቡና ምርታማነት በአማካይ ከ8 ነጥብ 5 ወደ 9 ነጥብ 2 ማደጉን ተናግረዋል።
በፍራፍሬ ምርትም አርሶ አደሮች በማኅበር በመደራጀት ምርታቸውን ለይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርት ኢንዱስትሪ ፓርክና ለአዲስ አበባ ገበያ እያቀረቡ ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙም አስረድተዋል።