የሕገ-ወጡን የህወሓት ቡድን እኩይ ተግባር በመቃወም የምናደርገውን ትግል አጠናክረን እንቀጥላለን - ኢዜአ አማርኛ
የሕገ-ወጡን የህወሓት ቡድን እኩይ ተግባር በመቃወም የምናደርገውን ትግል አጠናክረን እንቀጥላለን
አዲስ አበባ፤ ነሃሴ 1/2018 (ኢዜአ)፦ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን የሕግ የበላይነት እና ሥርዓት እንዳይኖር የሚፈጽመውን እኩይ ተግባር በመቃወም የምናደርገውን ትግል አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የትግራይ ክልል ወጣቶች ገለጹ።
ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን ለጦርነት በግዳጅ ከሚያደርገው አፈሳ አምልጠው የመጡ የትግራይ ክልል ወጣቶች ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በፖለቲካው መድረክ የተሸነፈው ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን ከተጠያቂነት ለማምለጥ እና ሥልጣኑን በሕገ-ወጥ መንገድ በኃይል ለማስቀጠል "ሕገ-አራዊት" በማውጣት ጦርነትን እንደ ብቸኛ አማራጭ አድርጎ በመውሰድ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም የክልሉ ተወላጅ ወጣቶች ህገ-ወጥ ቡድኑ እያካሄደ ያለው ከፍላጎት ውጪ የሆነ አፈሳ በመሸሽ ወደተለያዩ ክልሎችና ወደ ውጭ ሀገራት እየተሰደዱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወጣት ገብረ ኪሮስ ሕሉፍ ፤ ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን ሰላማዊ ሁኔታ ከተፈጠረ ተጠያቂነት ይመጣል ከሚል ስጋት እና ለሥልጣን ካለው ስግብግብነት በመነሳት ሕገ-መንግሥቱን እና የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በመጣስ የሕግ የበላይነት እና ሥርዓት እንዳይኖር እየሠራ መሆኑን አስረድቷል።
ቡድኑ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ትጥቁን ለመፍታት ቢስማማም ባለፉት ሦስት ዓመታት ስምምነቱን በመጣስ ታጣቂ ሲያሠለጥን እና ከውጭ ኃይሎች ጋር ጥምረት በመፍጠር ለጦርነት ሲዘጋጅ መቆየቱን ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅት ወደ አጥፊ ጦርነት ለመግባት ወጣቶችን ያለፍላጎታቸው በግዳጅ በማፈስ ወደ ጦር ካምፕ የማስገባትና ወደ ኤርትራና ሱዳን የመሸጥ ስራ ላይ ተጠምዶ እንደሚገኝ ጠቁሟል።
ወጣት ፀጋልኡል በርሔ በበኩሉ፤ የሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን በፖለቲካዊ መንገድ የተሸነፈ መሆኑን እና በአሁኑ ወቅት የሚፈጽማቸው የግዳጅ ወጣቶች ምልመላ፣ እናቶችን ማሰር፣ ግድያ እና የእንግልት ተግባራት የዚህ ውድቀቱ ማሳያዎች መሆናቸውን ገልጿል።
በዚህም ቡድኑ ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር ጥምረት በመፍጠር ወጣቶችን ለወታደራዊ ሥልጠና ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በአስገዳጅ ሁኔታ ከመላክና በተጨማሪ ወደ ኤርትራ እና ሱዳን እየሸጠ እንደሚገኝ ተናግሯል።
ቡድኑ እኛ በሥልጣን ላይ ካልኖርን ትግራይ ክልልንም ሆነ ሀገርን እናፈርሳለን በሚል አጥፊ አስተሳሰብ እየተመራ መሆኑንም አክሎ ገልጿል።
በመሆኑም የክልሉ ተወላጅ ወጣቶች ሕገ ወጥ ቡድኑ የሚያደርገውን ተግባር መቃወማችንን ማጠናከር አለብን ብለሏል።
የሕገ-ወጡ ህወሓት ቡድን መሪዎች የትግራዋይነትም ሆነ የኢትዮጵያዊነት ሥነ-ልቦና እንደሌላቸው እና አስተሳሰባቸውም ሆነ ተግባራቸው ፀረ-ትግራዋይነት እና ፀረ-ኢትዮጵያዊነት መሆኑን የገለጸው ደግሞ ወጣት ዮሐንስ ገብሩ ነው።
ትግራይ ክልልን በሕገ-ወጡ ቡድን ምክንያት ከገባችበት ሁለንተናዊ ቀውስ ለማውጣት ወጣቶች ተደራጅተው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አመልክተው፤ በግዳጅ ምልመላ እና በጦርነት ቅስቀሳ ላይ የምናደርገውን ትግል ማጠናከር አለብን ብለዋል።