የመደመር መንግሥት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በማሳደግ የዜጎችን ተጠቃሚነት በዘላቂነት እያረጋገጠ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በማሳደግ የዜጎችን ተጠቃሚነት በዘላቂነት እያረጋገጠ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ ነሃሴ 1/2018 (ኢዜአ)፦የመደመር መንግሥት አጠቃላይ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በፈጣንና ሁሉን አቀፍ የዕድገት ስልቶችን በመተግበር፣ የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በዘላቂነት እያረጋገጠ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የዕድሳት የማስፋፊያ ግንባታና ዲጂታላይዜሽን ሥራ ምረቃ እና ሥራ ማስጀመሪያ መርሃግብር ተከናውኗል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተመዘገቡ ያሉ የመሰረተ ልማት፣ የጤናና የተቋማት ማሻሻያ ስራዎች አበረታች ውጤት አስመዝግበዋል።
የመደመር መንግሥት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በፍጥነት ለማሳደግ ታስበው በተለዩ አምስት ቁልፍ ዘርፎች በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በዲጂታል አገልግሎቶች፣ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ከእነዚህ ዘርፎች የሚገኘው ሀብትና ኢኮኖሚ ዋና ዓላማው እንደ ትምህርትና ጤና ያሉ ማህበረሰባዊ ልማቶችን ማጠናከር እንደሆነ አብራርተዋል።
በጤናው ዘርፍ ከመከላከል በተጨማሪ አክሞ ለማዳን የሚያስችሉ ግብዓቶችና መድኃኒቶች ሀገር በቀል እንዲሆኑ በተሰሩ ሪፎርም ስራዎችም ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
እናቶች ከእርግዝና ጀምሮ እስከ ወሊድ እና ከወሊድ በኋላም ክትትልና እንክብካቤ አግኝተው ጤናማ ዜጋ እንዲፈጠር በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
መክፈል የማይችሉ ዜጎች ከጤና አገልግሎት እንዳይገለሉ የጤና መድን ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀው፣ ይህ በአፍሪካ ደረጃ አርዓያነት ያለው ስራ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ የህክምና አገልግሎትና የሆስፒታሎች ደረጃ ከፍተኛ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችንና ቁሳቁሶችን እያሟላ መሆኑን ተናግረው፤ ወደ ውጭ ሀገር ሄዶ የመታከም ፍሰትን ለማስቀረት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
የባህር ዳር ከተማ ውበትና መሰረተ ልማት ሲታከልበት ለወደፊቱ በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ትልቅ የህክምናና የቱሪዝም መዳረሻ እንደምትሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የተጀመሩ የዲጂታል አሰራርና የሪፎርም ስራዎች እስከ ዞን፣ ወረዳና ቀበሌ ድረስ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።