ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ለአሪ ዞን አርሶ አደሮች ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እየሆነ ነው

ጂንካ፤ ነሃሴ 1/2018 (ኢዜአ)፦የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ለአካባቢ ጥበቃ ካለው ፋይዳ ባሻገር ተጨማሪ የገቢ ምንጭ በመሆን ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን  በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአሪ ዞን አርሶ አደሮች ገለፁ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አሪ ዞን ደቡብ አሪ ወረዳ የጎምር ቀበሌ አርሶ አደር ታደሰ ሸዋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ አካባቢያቸው ተራራማና ተዳፋት በመሆኑ በተደጋጋሚ ለአፈር መሸርሸርና ለጎርፍ አደጋ ሲጋለጡ ቆይተዋል።

ባለፉት ዓመታት መንግስት የአካባቢውን አርሶ አደሮች በማሳተፍ በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች የአፈር መሸርሸርና ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭነታቸው እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸዋል።


 

የተፋሰስ ልማት በተከናወነባቸው አካባቢዎች ፍራፍሬ በማልማት በአሁኑ ወቅት ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ችግኝ በስፋት መትከል ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በአካባቢያቸው ተጨባጭ ለውጦች መታየታቸውን የገለጹት ደግሞ አርሶ አደር ገዛህኝ ገሚጋንሶ ናቸው።

ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር በተከናወኑ ተግባራት ያገኘነውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም በመገንዘብ ዘንድሮም ልማቱን አጠናክረን ቀጥለናል ያሉት አርሶ አደሩ፣ ልማቱ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ሙዝ፣ አቮካዶ እና ቡና ተክለው በማልማት ተጨማሪ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ጠቁመው፣  ይህን ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ በየዓመቱ በመርሀግብሩ የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል። 

አካባቢው በስፋት ቡና አብቃይ በመሆኑ ለእርሻ ሥራ ምቹ ባልሆኑ አካባቢዎች ጭምር ቡና ተክለው እያለሙ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው የቀበሌው አርሶ አደር ነሽራይ ከራልቆ ናቸው።


 

ባለፉት ዓመታት የተከሏቸው የቡና ችግኞች ምርት መስጠት እንደጀመሩ ጠቅሰው፣ ቡና ካስገኘላቸው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንጻር በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብርም በስፋት መትከላቸውን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል በአካባቢው በተራቆቱ አካባቢዎች የደን ችግኞችን ብቻ የማልማት ልምድ እንደነበር ያስታወሱት ደግሞ አርሶ አደር ማርታ ማቲዮስ ናቸው።

ለደን ልማት ብቻ የሚያገለግሉ ችግኞች ጥቅማቸው ውስን በመሆኑ አሁን ላይ ለምግብነት፣ ለአካባቢ ጥበቃ እና ለገቢ ምንጭነት የሚውሉ ችግኞችን ጭምር በማልማት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

የአሪ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጉራልቅ ይዥማልቅ በበኩላቸው እንዳሉት የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብርን ተከትሎ በዞኑ እንደ ፓፓያ፣ አቮካዶ፣ ማንጎ እና አፕል ያሉ ፍራፍሬዎች በስፋት እየለሙ ይገኛሉ።


 

ይህም የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ካለው ፋይዳ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን እያሳደገው መምጣቱን ተናግረዋል።

የሀገር በቀል ዛፎች እንደ ኮሶ፣ ዋንዛ፣ ጽድ እና ዝግባ ያሉና ሥነ-ምኅዳርን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ችግኞች በተራቆቱ ተራራማ አካባቢዎች በስፋት እየተተከሉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የአካባቢ ጥበቃ ሥራውን ከዘመናዊ የንብ ማነብ ሥራ ጋር በማስተሳሰር አርሶ አደሮች በዘርፉ ተሰማርተው ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ጉራልቅ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም