አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን እያረጋገጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን እያረጋገጠ ነው
አርባምንጭ ፤ ነሃሴ 1/2018 (ኢዜአ)፦የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት መርሃ ግብር የአካባቢያችንን ሥነ-ምህዳር በማስተካከል ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን እያረጋገጠ ነው ሲሉ የጋሞ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ።
በዞኑ የጋጮ ባባ ወረዳ የጋጼ ቀበሌ ነዋሪዎች አርሶ አደር አልቤ አለሙ እና አርሶ አደር አቡሽ አማሮ፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ለሰብል ምርትና ለእንስሳት መኖ ልማት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።
መርሃ ግብሩ የደን ዛፎችን በመትከል ገላጣ የነበሩ ተራሮች እንዲለሙ ማደረጉን ጠቁመው፤ የአቮካዶ፣ የማንጎ እና የአፕል ፍራፍሬ ችግኞችን በማልማት የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ ማስቻሉን ገልጸዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የደን ሽፋን እንዲጨምር በማድረጉ በንብ ማነብ ሥራ ተሰማርተው ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በምዕራብ አባያ ወረዳ የ«ጦይሎ» ንብ አናቢ ማኅበር ሰብሳቢ አቶ ደሴ ኡታሎ ናቸው።
ማኅበሩ በ52 አባላት በ2014 ዓ.ም መመስረቱን የጠቀሱት ሰብሳቢው፤ አሁን ላይ በ19 ሄክታር ደን ውስጥ ንብ ከማነብ ባለፈ የደን ጥበቃ ሥራ እያከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የሚያመርቱትንም ማር ለአካባቢው ገበያ በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ በማግኘታቸው አባላቱ በከተማ መኖሪያ ቤት መገንባታቸውንና የሸቀጥ ሱቆችን መክፈታቸውን ገልጸዋል።
የጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ማጌሶ ማሾሌ በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና ኢኮኖሚያዊ አቅምን በማሳደግ ረገድ ጉልህ ድርሻ እያበረከተ መሆኑን አስረድተዋል።
መርሃ ግብሩ የዞኑን የደን ሽፋን በማሳደግ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገሩ የልማት ስራዎች እንዲተገበሩ፣ እንዲሁም የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙ በማድረጉ የከርሰ ምድር ውሃ መጠንና የአፈር ለምነት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።
በዚህም ምርትና ምርታማነት ከመጨመሩም ባሻገር አርሶ አደሩ በንብ ማነብ ሥራ ተሰማርቶ ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻሉን አክለዋል።
በተጨማሪም በዞኑ የሚገኙ ተራሮች እየለሙ በመምጣታቸው በአባያና ጫሞ ሀይቆች ህልውና ላይ አደጋ እያስከተለ የነበረው የደለል አፈር በእጅጉ መቀነሱን አቶ ማጌሶ ገልጸዋል።